ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ለሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች 6 ሚሊየን 500 ሺ ብር የሚገመት የጤፍ ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ

ወልዲያ፤ ሰኔ 29 /2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በሰሜን ወሎ ለአርሶ አደሮች 6 ሚሊየን 500 ሺ ብር የሚገመት የጤፍ ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ።

በኮሚሽኑ የሰሜን ወሎ፤ደቡብ ወሎና ዋግ ኽምራ ኃላፊ አቶ ከሳ ተስፋ እንደገለጹት፤ የጤፍ ምርጥ ዘር ድጋፉ የአርሶ አደሮችን የአቅርቦት ችግር ለማቃለል የተደረገ ነው።

ድጋፉም ባለፈው ዓመት በአካበቢው በነበረው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው በሃብሩ፣ ራያ ቆቦና ጉባላፍቶ ወረዳዎች ለሚገኙ ወገኖች 687 ኩንታል የጤፍ ምርጥ ዘር መሆኑን አሰታውቀዋል።

ድጋፉ 9 ሺ 100 አርሶ አደሮችን ተደራሽ ማድረጉንና 370 ሄክታር መሬት ለመሸፈን እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ለአርሶ አደሮቹ በድጋፍ የቀረበው ምርጥ ዘር 6 ሚሊየን 500 ሺ ብር ግምት እንዳለው ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የግብዓት ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ደሳለኝ በበኩላቸው፤ በኮሚሽኑ የተደረገው ድጋፍ በጤፍ አምራችነታቸው ለሚታወቁት ሀብሩ፣ ጉባላፍቶና ራያ ቆቦ ወረዳ አርሶ አደሮች መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡

አምና በነዚህ ወረዳዎች አሸባሪው የህወሃት ቡድን በከፈተው ጦርነት የመኸር ምርት ለማምረት ሳይችሉ በመቅታቸው ለምግብም ሆነ ለዘር እጥረት ችግር ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቁንጮና ቦስት የተባሉ ምርጥ የጤፍ ዘር ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ማድረጉ የነበረባቸውን ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

ድጋፉም አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ሰብስበው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።  

ከሃብሩ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሰኢድ ጌትነት በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት በጦርነቱ ምክንያት በቂ ምርት ባለማግኘታችን የተነሳ ለዚህ መኸር ወቅት ምርጥ ዘር ለማግኘት ተቸግረን ቆይተናል ብለዋል።

የተደረገላቸው የምርጥ ዘር ድጋፍ ችግራችን ከማቃለሉም በላይ በመኽር ወቅቱ የተሻለ ለማምረት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

ሌላው አርሶ አደር ደምሌ እንድሪስ በበኩላቸው፤ የተራድኦ ኮሚሽኑ ያደረገልን የምርጥ ዘር ድጋፍ ወቅታዊና ችግራችንን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በጦርነቱ ምክንያት ያለ ምንም ምርትና ዘር በመቅረታቸው በዘንድሮው መኸር የሚዘሩት አጥተው እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን በተደረገልን ድጋፍ በቂ ምርት በማምረት የምግብ ዋስትና ችግራችን ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ጠቅሰው፤ የቀጣይ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግራችንም የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም