ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠናከር በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል - ጉባኤው

ሚዛን አማን፤ ሰኔ 29/2014 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ልዩነቶችን በማክበር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠናከር ትኩረት ሰጥተው በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስረታና የምክክር መድረክ  በሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ነው።  

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉኋን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ፤ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በውስጥና በውጭ ጠላቶች በጽኑ እየተፈተነች መሆኗን ተናግረዋል።

" በዚህ ፈተና ወቅት የሃይማኖት ተቋማት ልዩነቶችን በማክበር ለኢትዮጵያ ሰላምና አብሮነት መጠናከር ትኩረት ሰጥተው በጋራ መስራት አለባቸው" ብለዋል።

የሃይማኖት ሰዎች በፈተና ሳይዋዥቁ የመጽናት ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በመያዝ ፀንተው በሀገራችን እየታየ ያለው ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቋጭ ከልብ በመጸለይ መትጋት አለባቸው ነው ያሉት።

መልካም ነገሮችን ሁሉ ያለስስት በማድረግ የበኩላችንን አዎንታዊ ሚና በኢትዮጵያ ሰላም ላይ ማሳደር አለብን ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

የሃይማኖት ተቋማትና አማኞች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በማክበር በጋራ ጉዳይ ላይ መተባበርና መደጋገፍ እንደሚኖርባቸውም አመላክተዋል።

ጉባኤው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሚያግባቡ ሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በመስራት ግጭቶች እንዳይከሰቱና አብሮነት እንዲጎለብት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በግጭቶች ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ፈጥኖ ለማስተካከል ጉባኤው እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው፤ የሀገራችን ህዝቦች የእምነት ልዩነት ሳይገድባቸው የጋራ ባህልና ወግ በመያዝ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብና አብሮነትን በመያዝ ለዘመናት የቆዩ ናቸው ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት የሰላም፣ የፍቅርና አብሮነት ትምህርት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በመጥቀስ ፤ ይህንን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

አልፎ አልፎ የሚታዩ ከሃይማኖት አስተምህሮ ያፈነገጡ የልዩነትና ጥላቻ ድርጊቶች እንዲወገዱ የሃይማኖት መሪዎች ተቀራርበው  መፈተሽ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

"በተለይ ጥቃቅን ችግሮች ሰፍተው ሰፊ ግጭትና ጉዳት በእምነቶች መካከል እንዲፈጠር ሆን ብለው የሚሰሩ ፀረ ሰላም አካላትን ተግባር በማክሸፍ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በየአካባቢው መስራት አለበት" ብለዋል።

በክልሉ ለሚመሰረተው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቢሮና በሌላም ለመደገፍ የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሁሉንም የእምነት ተቋማት በእኩል በማየት ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ተቀራርበን እንሰራለን ብለዋል ዶክተር ነጋሽ ።

ጉባኤ በምስረታ መርሐ ግብሩ ከየእምነት ተቋማት ለተወከሉ የቦርድ ሥራ አስፈጻሚዎች የሥራ ክፍፍል እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በቀጣይም በሀገራዊ የሰላምና አብሮነት ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም