ቢሮው በጦርነቱ ምክንያት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የአፋር ክልል ልዩ ኃይል አባላት የአካል ድጋፍ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው በጦርነቱ ምክንያት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የአፋር ክልል ልዩ ኃይል አባላት የአካል ድጋፍ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ
ሰመራ፣ ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፋር ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በጦርነቱ ምክንያት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸዉ 50 የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት የአካል ድጋፍ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አሊ ዘይን ለልዩ ኃይል አባላቱ ድጋፉን አስረክብዋል። ድጋፉ የ30 የአካል ድጋፍ ክራንች እና 20 ዊልቸር ነው።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ደቅኖት የነበረውን አደጋ ለመቀልበስ የአፋር ክልል አርብቶ አደር ማህበረሰብና የጸጥታ መዋቅሩ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን የቢሮው ኃላፊ አስታውሰዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች እንዲያገግሙ ቢሮው ከመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም መሰል ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረው፤ በጦርነቱ ምክንያት ስነ ልቦናዊ፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች መደገፍ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ እንደሆነም አመልክተዋል።
የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ተወካይ መቶ አለቃ አረብ መሀመድ በበኩላቸዉ ልዩ ኃይሉ ከክልል የጸጥታ መዋቅርና ሕብረተሰቡ ጋር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አሁንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው ብለዋል።
የክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤