ቀጥታ፡

የኢጋድ አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ በቀጣናው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት መግባባት ላይ የተደረሰበት ነው

ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) 39ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ በቀጣናው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተናገሩ፡፡

የኢጋድ መሪዎች 39ኛው አስቸኳይ ስብሰባ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ትናንት ተካሂዷል።

በጉባኤው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህምድ እንዲሁም ሌሎች የአባል ሀገራቱ መሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በ39ኛው የመሪዎቹ ጉባኤ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የቀጣናው አገራት ውስጣዊና ዓለም አቀፋዊ አዳዲስ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አባል አገራቱ እነዚህን ችግሮች እንደ አንድ ቤተሰብ በትብብር መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የገለጹት፡፡

በቀጣናው ያሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ አደጋዎችን በተናጠል ጥረት በዘላቂነት መፍታት እንደማይቻልም ነው የተናገሩት፡፡

ፈተናዎቹን ከመሻገር ጎን ለጎን በቀጣናው ያሉ መልካም የጋራ ተጠቃሚነት እድሎችን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባም እንዲሁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፤ ጉባኤው ድርቅን ጨምሮ ቀጣናውን እየፈተኑ በሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በትብብር መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረጉን አንስተዋል፡፡

እነዚህ አደጋዎች ድንበር ሳይገድባቸው ሁሉንም አባል አገራት የሚጎዱ መሆናቸውን አንስተው፤ የቀጣናው አገራት በኢጋድ አማካኝነት በመተባበር መፍትሄ ማምጣት እንዳለባቸው መሪዎቹ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

ችግሮችን በመከላከል ረገድ ከዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባም አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው የተሳተፉ የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በቅርበት እየተወያዩ የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሔዎችን ለማምጣት መወሰናቸውንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት፡፡

በጉባኤው የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በአፍሪካ ህበረት ጥላ ስር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ያሳየውን ቁርጠኝነት ኢጋድ ማድነቁንም ተናግረዋል፡፡

ኢጋድ የኢትዮጵያ መንግስት ለጀመረው የሰላም አማራጭ ውጤታማነት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጡንም ነው የጠቀሱት፡፡

በተጨማሪ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን  እያደረገ ያለው ጥረት አድናቆት ተችሮታል ነው ያሉት።

ኢጋድና አባል አገራቱ ቀጣናውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሰፈነበት ለማድረግ መስራት እንዳለባቸውም ነው በጉባኤው አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልኮዋን በብቃት በመወጣት ጭምር ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይህንን ስራ አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን በጉባኤው አረጋግጣለች ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ሶማሊያን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ሱዳንና ኡጋንዳን በአባልነት የያዘ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም