ቀጥታ፡

ሰራዊቱ በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ችግኝ እየተከለ ለትውልድ አሻራውን እያኖረ ነው-ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ

ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ሰራዊቱ በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ችግኝ እየተከለ ለትውልድ አሻራውን ያኖራል" ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት በቢሸፍቱ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ግቢ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን እያስቀመጡ ነው።

አራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 'አሻራችን ለትውልዳችን' በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቷ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ የዓለም ፍጥረታት በአየር ንብረት ለውጥ እየተቀጡ መሆኑን ጠቅሰው ሁላችንም ለአረንጓዴ ልማት በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ችግኝ እየተከለ ለትውልድ የሚሻገር አሻራውን እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከላከል ያለመ ስራ መሆኑን አንስተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመሰገነ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል የህዝብ ድጋፍ ያለው መሆኑን የገለጹት ሌትናል ጄነራሉ፤ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላትም በአየር ኃይል ግቢ በመገኘት ላደረጉት መልካም ተግባር አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለአገር ሉአላዊነትና ለህዝቦች ሰላም ማስከበር ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቃድር፤ የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር እያደረገ ላለው ተጋድሎ ከበሬታና አድናቆት ለመስጠት ተገኝተናል ብለዋል።

በአየር ኃይል ግቢ በመገኘት አሻራችንን በማኖራችንም ታላቅ ደስታ ይሰማናል ነው ያሉት።

የምክር ቤቱ አባላት የአረንጓዴ አሻራቸውን ካኖሩ በኋላ በእለቱ የቤት ዕድሳት አስጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም