የኢራንን የእደ-ጥበብና ሥነ -ጥበብ ስራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢራንን የእደ-ጥበብና ሥነ -ጥበብ ስራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ )የኢራን የእደ- ጥበብና ሥነ- ጥበብ ስራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሙዚየም ተከፍቷል።
አውደ-ርዕዩ የተከፈተው በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሰመድ አሊ ላኪዛዴህ እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ነው።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ርዕይ በተለያዩ ንድፎች የተሰሩ የሸክላ ውጤቶች፣ የስዕል ስራዎች እንዲሁም ምንጣፎችን ጨምሮ የተለያዩ የእደ-ጥበብ ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል።
በአውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያና ኢራን በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ነው የተነሳው።
በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሰመድ አሊ ላኪዛዴህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አውደ ርዕዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት የባህል ትስስር ለማጠናከር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የተሳናዳ ነው።
ለአውደ ርዕዩ መሳካት ከተማ አስተዳደሩ ሊመሰገን እንደሚገባም ነው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት።
ሁለቱ አገራት ዲፕልማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 50 ዓመት እንደሆናቸው ያስታወሱት አምባሳደሩ የዚህ አውደ- ርዕይ መዘጋጀት የአገራቱን ግንኙነት እንደሚያጠናክርም ጠቅሰዋል።
የአውደ-ርዕዩ መዘጋጀት በተለይም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ አወንታዊ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ባህላዊና ሥነ- ጥበብ ስራዎች በኢራን እንዲቀርቡ ዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል።
በባህል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ ኢራን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለባህል ቅድሚያ መስጠቷን ተናግረዋል።
ሁለቱ አገራት በባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ዘርፍ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ከዚህ በፊት መፈራረመማቸው ይታወሳል።