ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መወሰኗን የኢጋድ መሪዎች አደነቁ

ሰኔ 28/2022 /ኢዜአ/ የኢጋድ መሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መወሰኑን እንዲሁም አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት አደነቁ።

መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ እያደረገ ያለው ጥረትም በመሪዎቹ ጉባኤ አድናቆት ተችሮታል።

39ኛው የኢጋድ መሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ፖለቲካዊ ለውጦች፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ሲመክር ውሏል።

በጉባኤው የተሳተፉ መሪዎች የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባቸውን አጠናቀዋል።

በጋራ መግለጫቸውም አዲስ ለተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሶማሊያውያን በዴሞክራሰያዊ መንገድ መሪያቸውን በመምረጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ የነበራቸውን ሚና አድንቀዋል።

የመሪዎቹ መግለጫ በኢጋድ አባል ሀገራትና በቀጣናው ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ የሚገኙ ውስጣዊና ውጫዊ የፖለቲካና የደህንነት ችግርችንም በጋራ መቋቋምና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራ መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቷል።

መግለጫው ሱዳናውያን ሀገራዊ ችግሮቻቸውን አካታችና በራሳቸው ባለቤትነት በሚመራ መልኩ ለመፍታት እያደረጉ ያሉት ጥረት ተጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የመሪዎቹን አቋም አንጽባርቋል።

በኢጋድ፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነትም በተለያዬ ጎራ የተሰለፉ ሱዳናውያን ውይይት እንዲያደርጉ የተጀመሩ ተግባራትንም በበጎ ተመልክቷቸዋል።

የኢጋድ መሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መወሰኑን እንዲሁም አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት በመግለጫቸው አድነቀዋል።

መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ እያደረገ ያለው ጥረትም በመሪዎቹ ጉባኤ አድናቆት ተችሮታል።

ኢጋድ ኢትዮጵያ ዘላዊ ሰላምን ለማስፈን እያደረገች ያለችው ጥረት እንዲሳካ አወንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ነው የተገለጸው።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት የሽግግር ጊዜ ስምንት ወራት እንደቀረው ያተተው የመሪዎቹ መግለጫ የሰላም ሂደቱን እውን ለማድረግ አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቁ ጠቁሟል።

በመሆኑም የሽግግር ጊዜ የአንድነት መንግስቱና የሚመለከታቸው አካላት የሰላም ሂደቱን የሽግግር ጊዜ እውን ለማድረግ የሚቀሩ ተግባራትንና ምርጫ የሚካሄድበትን አጠቃላይ ሁኔታና የጊዜ ሰሌዳ ያካተተ ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁ አሳስቧል።

መግለጫው መሪዎቹ በድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ በጥልቀት መምክራቸውን ጠቅሶ በቀጣናው ያለውን ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ለመመከት የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሔዎችን በጋራ በማዘጋጀት መስራት እንደሚገባ ጠቁሟል።

በቀጣናው በድርቅና በሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ፈተና ላይ የወደቀውን የምግብ ዋስትና ጥያቄን ምላሽ ለመስጠትም የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ እንዲሁ።

በጉባኤው በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ወደ ቀጣናው የሚፈሰው የምግብ አቅርቦት ላይ እጥረት መከሰቱ የተነሳ ሲሆን፤ ኮቪድ 19 በጤና ስርዓቱ ላይ የፈጠረው ጫና እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች ያለው ከባድ የጎርፍ አደጋ አሳሳቢ በመሆኑ የተቀናጀ አስቸኳይና ዘላቂ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ተነግሯል።

ዓለም አቀፍ አጋሮችና የረድኤት ተቋማት ሰብዓዊ ድጋፋቸውን አጠናክርው እንዲቀጥሉ በመሪዎች ጉባኤ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም