ቀጥታ፡

በሰላማዊ መንገድ በሀሳብ ልዕልና ማሸነፍ ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 ሰንደቅ ዓላማን ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ በሀሳብ ልዕልና ማሸነፍ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ከውጭ እየገቡ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዓርማቸውንና ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ለህዝባቸው መንገር ይችላሉ ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ አሸንፎ ሌላው የሚሸነፍበት የፖለቲካ ስርዓት ይበቃናል ብለዋል። ከውጭ እየመጡ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በተረጋጋ ስሜት በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማሸነፍ አለባቸው ነው ያሉት። ከውጭ እየገቡ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አሸናፊ ናቸው እኛም አሸናፊ በመሆናችን ነው እየተቀበልናቸው ያለነው ያሉት ዶክተር አብይ ነገር ግን አሸናፊነትና መሪነትን መለየት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። "አሁን እየታየ ያለው ስሜታዊነት ሰው ወደ ልቦናው ሲመለስ ይቀጥላል ብላችሁ እንዳታስቡ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ህዝብ ህገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ ተወያይቶ መክሮና ዘክሮ ሊቀይር ይችላል" ብለዋል። መንግስት አሁን እየተፈጠረ ያለውን ችግር በኃይል መመለስ አቅቶት ሳይሆን ሁሉም ነገር በፍቅርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም