ቀጥታ፡

ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንዲሆኑ ማጠናከር ያስፈልጋል - አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ሰኔ 28/2014 (ኢዜአ) የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ማሟላት እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ ፡፡

“የዛሬ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የነገ ኢንዱስትሪያሊስቶች ናቸው ” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ያዘጋጀው ባዛርና ኢግዚቢሽን በሀዋሳ ከተማ ተከፍቷል ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደገለፁት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም ማጠናከር ያስፈልጋል።

"ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሀሳብ ኢንዱስትሪዎችን የማበረታታት ዘመቻ መጀመሩን አንዱ የማጠናከሪያ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

"በተለይ እንደ ሲዳማ ክልል የመሬት ጥበት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ሰፋፊ የሰው ኃይል ሊይዙ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ቁልፍ ተግባር ነው "ብለዋል።

አሁን ያሉ ኢንተርፕራይዞች ብቁ ሆነውና አድገው ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ በመሸጋገር የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንዲሆኑ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የክህሎት ማደበሪያ ሥልጠናን በማጠናከር የሚያመርቷቸውን ምርቶች ጥራትና ብዛት እንዲያሳድጉ መስራት  እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል ፡፡

ምርቶቻቸውን በመግዛት ማበረታታት እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ለመንግስት ተቋማት ምርቶቻቸውን  እንዳያቀርቡ የሚያግዱ አሰራሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለማስተካከል ጥረት እንደሚያደረጉ ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ የሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረፅዮን አበበ በክልሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ዕድል መፍጠር የሚያስችላቸው ባዛሮችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል ፡፡

እንደ ኃላፊዋ ገለፃ ኢንተርፕራይዞች በራሳቸው መንገድ ገበያ ፈጥረው ከሚያገኙት ገቢ ባሻገር በመንግስት በኩል በበጀት ዓመቱ የ348 ሚሊዮን ብር የገበያ ዕድል መመቻቸቱን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ካሉት 5 ሺህ 881 ኢንተርፕራይዞች መካከል ከ500 በላይ የሚሆኑት ዘንድሮ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ናቸው ብለዋል።

ለአዲሶቹ ኢንተርፕራይዞች ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ከ198 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረብ እንደተቻለም ገልጸዋል ፡፡

የክህሎትና ሌሎች ክፍተቶቻቸውን ለመሙላት ከሚሰጣቸው ሥልጠና ባሻገር ድጋፍ የሚያደርጉላቸው የቴክኒክና ሥልጠና ተቋማትን የማጠናከር ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል ፡፡

በባዛሩ ከተሳታፉ ኢንተርፕራይዞች መካከል የአኪያ ጥልፍና ስፌት ማህበር አባል ወጣት ድንበር ከተማ እንዳለችው ባዛሩ የገበያ ዕድሎችን ከማስፋት ባሻገር እርስ በርስ ልምድ ለመካፈል ይረዳል ፡፡

የክህሎት ሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሳ ወደ ጨርቃጨርቅና ኢንዱስትሪ ደረጃ የመድረስ ህልማቸውን ለማሳካት የማሽነሪ ብድር አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጠይቃለች፡፡

በኤግዚቢሽኑ ላይ 142  ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ማቅረባቸውንና እስከ ሐምሌ 2/2014 ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም