የጋራ ተጠቃሚነት ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ተጠቃሚነት ማሳያ
(በሳሙኤል አየነው-አርባ ምንጭ)
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 21/1997 በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሂደት ባወጣው ኮንቬንሽን መሰረት የተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊ የአጠቃቀም መርህን ተከትለው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ የተፋሰሱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶች፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሁኔታና የአንዱ መጠቀም በሌላኛው የተፋሰስ ሀገር የጎላ ተጽዕኖ አለማሳረፉን በመስፈርትነት ማካተቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ለዘመናት የኤሌክትርክ አቅርቦት የሌላቸውና ከጭስ ያልተለዩ 60 በመቶ የሚሆን ህዝቦቿን የያዘች ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን ለኤሌክትሪክ ሃይል ለማዋል በቁጭት በመነሳት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ አድርሳለች። የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ታሳቢ በማድረግም ለተከታታይ ሁለት ክረምቶች ግድቡን ውሃ የሞላችና አንድ ተርባይን ሃይል እንዲያመነጭ ያደረገች ሀገር፤ በያዝነው ክረምት ሶስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወንና ሁለተኛውን ተርባይን ሃይል እንዲያመነጭ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች ነው።
ግብጽና ሲዳን በኢንግሊዝ አርቃቂነት ኢትዮጵያን በማግለል የተዋዋሉትን የ1929 እና የ1959 ውሎች ነፍስ እንዲዘሩ ግብጽ የቻለችውን ሁሉ ከማድረግ አልቦዘነችም፡፡ ሀገራቱ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሂደት ኮንቬንሽን ስምምነት ለመመራት ቢፈልጉ ኖሮ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ወጪ 20 በመቶ ሱዳን 30 በመቶ ደግሞ ግብጽ መሸፈን ይገባቸው ነበር፡፡ ግብፅ ከዚሁ ትብብር ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር ጥረቷን ቀጥላለች፡፡
በየነ አፈዬ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ሃይል ምርምር ማዕከል ተመራማሪና መምህር ናቸው። አቶ በየነ አፈዬ የገጠሩን ማህበረሰብ የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ ድንጋሞ ቀበሌ ከ400 እስከ 600 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጥናት አከናውነዋል። ጥናቱን ወደ ተግባር ለመቀየርም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወቃል፡።
ምሁሩ ''የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ግብፅን ለውሃ እጥረት ይዳርጋል ተብሎ የሚወራው የግብፅ ፓለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃን ሴራ እንጂ እውነታውን የተከተለ አይደለም'' ይላሉ፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለጻ ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚዋ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ማዋል ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣትና መሰል ተስፋ ሰጭ የልማት እንቅስቃሴዎች የኃይል ፊላጎቱ እንዲያድግ ማድረጉንና እንደ ሀገር ያለው የኃይል አቅርቦትና የህዝቡ ፍላጎት የማይጣጣም መሆኑን አመልክተዋል።
''ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ግዙፉን የአስዋን ግድብ በመገደብ እስከ ዛሬ ስትጠቀም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን አንፃር አልከለከለቻትም'' ያሉት አቶ በየነ፤ 86 በመቶ የአባይ ወንዝ ባለቤት የሆነችው ሀገር የአባይ ወንዝን መጠቀምና ማልማት መብቷ የተጠበቀ መሆኑን ያስረዳሉ።
አቶ በየነ የአባይን ወንዝ ለኃይል አገልግሎት መዋሉ ጥቅሙ ዘረፈ በዙ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ የወንዙ ፍሰት ክረምት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር በመሆኑ ለተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ለሱዳንና ግብፅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ከሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ጋራ ጎን ለጎን መከናወኑ ዘላቂ ጥቅሙን የጎላ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።፡
ምሁሩ እንደሚሉት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በአስዋን ግድብ ላይ ሲደርስ የነበረው የጎርፍና ደለል አደጋ የሚያስወገድ ነው፡፡ በተለይም በአስዋን ግድብ ላይ የውሃው መጠን ከአቅም በላይ በሚሆንበት ጊዜ ግድቡን በማስተንፈስ ውሃውን በሚለቁበት ጊዜ በትነት ምክንያት የሚባክነውን ከፍተኛ የውሃ መጠን መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
የአስዋን ግድብ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት አከባቢ መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ፤ ይህም ከፍተኛ የውሃ መጠን በትነት እንዲባክን እንደሚደርግ አመልክተዋል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለበት ቦታን ተከትሎ በሚሰራው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአባይ ውሃ በትነት እንዳይባክን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ''የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ የከባቢውን አየር በመቀየር የከርሰ ምድር ውሃ መጠንን በመጨመር የቀጠናውን ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል›› ብለዋል፡፡
ውሃው የግድቡን ተርቫይን በመምታት ኃይል ካመነጨ በኋላ ወደ ቀድሞው ፍሰቱ የሚመለስ በመሆኑ የታችኞች ተፋሰስ ሀገራትን የሚጎዳ አንዳች ምክንያት የለውም ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ደመላሽ ወንድማገኘው ናቸው፡፡
''ግብፅና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው ተቃውሞ የኢትዮጵያን ዕድገት ለማደናቀፍ እንጂ ሳይንሳዊ ምክንያት የላቸውም'' ብለዋል፡፡ኢትዮጵያ 86 በመቶ የወንዙ ባለቤት ሆና ይህንን የተፈጥሮ ፀጋ ብቻዬን እጠቀማለሁ ከማለት ይልቅ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ረገድ ዓለም አቀፍ መርህን ማክበሯም ተገቢና በጋራ ለመልማትና ለመጠቀም ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ክረምትን ጠብቆ በየአመቱ መደረጉ ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብን በታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ላይ ተጽዕኖ በማይፈጥር መልኩ ለማከናወን ያላትን ዝግጁነትና ጽኑ ፍላጎት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ በኢኮኖሚ የቀጠናውን ሀገራት የሚያስተሳስር በመሆኑ የሀገርን አንድነትና ትስስር ሂደት ከፍ እንደሚያደርግ ተጠቁመዋል፡፡ በዓለም አቀፍ መርህ መሰረት ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ የሚፈሱ ወንዞችን በፍትሃዊ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል እንደ ተቻለ፤ ኢትዮጵያም ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር የአባይን ወንዝ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንጠቀም ማለቷ በበጎ ጎኑ ሊታይ የሚገባውና ግብጽና ሱዳን ከውሃውም ሆነ ግድቡ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ልማት በሀሳብም በገንዘብም መደገፍ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።
ግብፅ ከአስዋን ግድብ በተጨማሪም 550 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የናስር ሐይቅ በመገንባት አየተጠቀመችና ለ500 ዓመታት የሚያገለግል በከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እጅግ የበለጸገች አገርም መሆኗን የሚያመለክቱት ምሁሩ፤ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው ተቃውሞ ፖለቲካዊ እንጂ ሳይንሳዊ ምክንያት የለውም ብለዋል። የግድቡን 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ብሎም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምሁራኑ ጠይቀዋል።
ከፊታችን ሁለት አማራጮች አሉን፤ አንድም የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁሞ የምንጊዜም ጠላታችን በሆነው ድህነት ላይ ድል በመቀዳጀት የኢትዮጵያን እድገት ማረጋገጥ አልያም በውስጥና በውጭ ጫናዎች በመንበርከክ ለድህነት ባሪያ ሆኖ መቅረት። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ሽንፈትን መቼም ቢሆን አቤት ወዴት ብለው ሊቀበሉት እንደማይችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለሆነም እስካሁን የተለያዩ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ ሀገራቸው ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም፣ነገም፣ ወደፊትም በፈተና እያለፉ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ሀገርን ወደ ከፍታ የሚወስዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እያጠናቀቁ የሀገርን ህልውና አስጠብቀው ይጓዛሉ።ሰላም።