ቀጥታ፡

መንግስት በየቀኑ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ ነው

ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት በየቀኑ በአማካይ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ በሃምሌ ወር በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ይኖራል በሚል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የምጣኔ ሃብት አሻጥር የሚፈጥሩ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድም አሳስቧል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ከባለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት መንስኤ አቅርቦት ሳይሆን በስርጭት ላይ በሚፈጸሙ ችግሮች እንደሆነ ተረጋግጧል።

ቀደም ሲል በየወሩ መጨረሻ ቤንዚን ላይ እጥረት ይከሰት እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ባልተለመደ ሁኔታ በናፍጣ ላይ የተከሰተው እጥረት የአገርን ሃብት ለግል ጥቅም ለማዋል የተደረገ አሻጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በባለፉት ሶስት ወራት መረጃ መሰረት ከጂቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የነዳጅ አቅርቦት በየወሩ እየጨመረ ነው ብለዋል።

በዚህም መንግስት በአሁኑ ወቅት በየቀኑ በአማካይ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።

May be an image of 3 people and road

በተለያዩ ቦታዎች ቆመው የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ ቦቲዎች ነዳጁን በፍጥነት ወደ ማደያ በማድረስ እንዲያሳውቁ የተላለፈውን ውሳኔ ያላከበሩ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በዚህም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውሳኔውን ያላከበሩ 10 የነዳጅ ቦቲዎች መወረሳቸውን ተናግረዋል።

በመንግስት ቁጥጥር ስር የገቡ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ "ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን ንብረት ወይም እቃ መከዘን" በሚል የወንጀል ህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በማደያዎች በኩልም ነዳጅ እያለ የለም የማለት፣ የማሸሽ፣ የመያዝና ሌሎች ችግሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን፤ ከጅቡቲ በአማካኝ በየቀኑ 300 የነዳጅ ቦቴ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ በጅቡቲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅንጅት ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነዳጅን በ73 ብር ከውጭ ገዝታ 40 ብር ድጎማ በማድረግ ከ35 እስከ 36 ብር እየሸጠች ትገኛለች።

May be an image of 3 people and car

በዚህም መንግስት በአንድ ዓመት 132 ቢሊዮን ብር ለድጎማ ወጪ ያደረገ ሲሆን፤ ድጎማ በዝቅትኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ህብረተሰብ ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም በከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ደረጃ ያሉትንም ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።

ከሃምሌ ወር 2014 ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ለመተግበር በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እየተዘረጋ ነው።

የቴክኖሎጂ አሰራሩን እውን ለማድረግም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ኢትዮ ቴሌኮም ትናንት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

በነዳጅ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ተግባራዊ ሲደረግ ከማስተካከያው በፊት የተጓጓዘው ነዳጅ ቀድሞ በነበረው ዋጋ እንዲሸጥ አስገዳጅ ሁኔታ መቀመጡንም ወይዘሮ ሳህረላ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም