በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሃብቶችን በወርቅ፣ እምነበረድ፣ ከሰል ድንጋይ እና ሌሎችም ማዕድን ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲገቡ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሃብቶችን በወርቅ፣ እምነበረድ፣ ከሰል ድንጋይ እና ሌሎችም ማዕድን ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲገቡ ተደርጓል

አሶሳ፣ ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሃብቶችን በወርቅ፣ እምነበረድ፣ ከሰል ድንጋይ እና ሌሎችም ማዕድን ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲገቡ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።
በክልሉ ባለሃብቶችን በተፈጥሮ ሃብት ልማት በስፋት እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፤ በማዕድን ልማት ዘርፍ በተደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ለ183 ወርቅ አምራቾች ፈቃድ ተሰጥቷል።
ይህ ቁጥር ከአምስት አመታት በፊት 86 ብቻ እንደ ነበር ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም የባህላዊ ወርቅ አምራቾች ማህበራት ቁጥር ባለፉት ሶስት ዓመታት ከነበረበት 26 በበጀት ዓመቱ ወደ 234 አድጓል፡፡
በቤኒሻንጉል ክልል ወርቅ አምራቾችን እና አዘዋዋሪዎችን ለማበረታት እንዲሁም ለማመስገን በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ዝግጅት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንዳሉት፤ በክልሉ የተፈጥሮ ሃብትን ለሀገር ኢኮኖሚ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም ባለሃብቶችን በስፋት ወደ ወርቅ፣ እምነበረድ፣ ከሰል ድንጋይ እና ሌሎች የማዕድን ልማት እንዲገቡ ማድረግ ዋነኛው ትኩረት መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም እያደገ የመጣውን የመካከለኛ እና አነስተኛ ወርቅ አምራች ማህበራት ቁጥር ማሳደግ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ሌላው የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም አመልክተዋል።
በተለይ በአሶሳ ዞን የሚገኙ ባህላዊ አምራቾች ለወርቅ ማምረት ኬሚካል እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው በሳይንሳዊ መንገድ ካልተደገፈ በሰው፣ በእንስሳት እና በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጦ የሚወጣ ወርቅ መኖሩን የጠቀሱት ርእሰ መስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ የተጀመሩ እርምጃዎች እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል።
የክልሉ ማዕድን ልማት አጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ናስር መሃመድ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት አመታት የወርቅ እና የሌሎች ማዕድናት ምርት በከፍተኛ መጠን መጨመሩን አስረድተዋል፡፡
የማዕድን ምርት ሊጨምር የቻለው መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ውጤቱ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል::
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ