በሲዳማ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መሰጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መሰጠት ተጀመረ
ሀዋሳ፣ ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መሰጠት ተጀመረ፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮው ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ እንዳሉት በሲዳማ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተና በሁሉም ጣቢያዎች መሰጠት ተጀምሯል ፡፡
አቶ በየነ በለኩ ከተማ ሞሮቾ ሾንዶሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የፈተናውን መጀመር ተመልክተዋል፡፡
ፈተናው በክልሉ በሚገኙ 774 ትምህርት ቤቶች መሰጠት መጀመሩን አብራርተዋል፡፡
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች በተገቢው ትምህርታቸውን በመከታተል ሲዘጋጁ የቆዩ ከ81 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎች ፈተናውን መውሰድ መጀመራቸውን ገልጸዋል ፡፡
ፈተናውን በተቀናጀ መንገድ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አቶ በየነ ገልጸዋል፡፡
የፈተናን ከኩረጃ ነጻ የመሆን ደህንነት ለማረጋገጥ የመምህራንና የሱፐርቫይዘሮች ድልድል መካሄዱን አክለዋል።
ከጸጥታ ሃይሎች ጋርም በቅንጅት የፈተና ወረቀት ስርጭት መከናወኑን ገልጸዋል ፡፡
በአንድ ክፍል 25 ተማሪ እንዲቀመጥ ታሳቢ በማድረግ ከ3 ሺህ300 በላይ ፈታኝ መምህራን መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ