የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወጣቶች በታላቅ ሃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል - ዶክተር ዓለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወጣቶች በታላቅ ሃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል - ዶክተር ዓለሙ ስሜ
ደብረ ብርሃን ፤ ሰኔ 27/ 2014 (ኢዜአ) ሃገርን ለማፍረስ በውስጥና በውጭ ሀይሎች የተቃጣብንን ጥቃት እንደመከትነው ሁሉ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወጣቶች በታላቅ ሃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አባላት በደብረ ብርሀን ከተማ በአፄ ዘረ ዓያቆብ ክፍለ ከተማ አንድነት ቀበሌ 4ኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ችግኝ ተከላ አካሄደዋል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ በወጣቶች ጠንካራና ያልተቋረጠ ትግል ሀገራዊ ለውጥ መምጣቱን አውስተዋል።
ይህ ያልተዋጠላቸው የከፈቱብንን ጥቃት ለማክሸፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሚና የላቀ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁንም የኢትዮጰያን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ወጣቱ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የተጋረጠባትን ፈተና በንቃት ከመመከት ባለፈም በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በስፋት መሳተፍ እንዲሁ።
የአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስኬታማ እንዲሆን ከመስራት ጎን ለጎንም በኢኮኖሚው ዘርፍ ወጣቶች ያልታረሱ መሬቶችን በየአካባቢያቸው በማልማት የኑሮ ውድነት እንዲረጋጋም የበኩላቸው ሚና እንዲወጡም ተናግረዋል።
እንዲሁም ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የተሳካ እንድሆን ወጣቶች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ዶክተር አለሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አስፋው ተክሌ በበኩሉ፤ ዘንድሮ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሊጉ አባላትና ደጋፊዎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግንባር ቀደም ሆነው እንደሚሳተፉ ገልጿል።
በዋነኛነት የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመጠገንና ቁሳቁስ በማሰባሰብ መደገፍ፣ በትምህርት፣ በጤና፣በደም ልገሳና መሰል የልማት ስራዎች በስፋት ይሳተፋሉ ብሏል።
እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቋል።
የሊጉ አባላትና ደጋፊዎችም አሁን ላይ የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስቧል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት ባርዱለህ ኦሊኪቦ፤ በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡትን ሁለተናዊ እድገቶች ዘላቂ ለማድረግና የወጣቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንሰራለን ብሏል።
አንድነታችንን በማጠናከር ሀገራዊ ብልፅግናችንን እውን እናደርጋለን ያለው ደግሞ የአማራ ክልል ወጣቶች ሊግ ምክትል ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት አብይ አበባው ነው።
ከጋምቤላ ክልል የመጣችው ወጣት አባንግ ኩሙደን፤ የሀገራችንን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ወጣቶችን በማስተባበር እሰራለሁ ብላለች።
በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ችግኝ ተከላ ላይ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ የሊጉ አባላትና ሌሎችም አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።