ቀጥታ፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገበር ነው

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገበር መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት  እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን በጋራ ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

በሀገሪቱ እስካሁን በተግባር ላይ ያለው የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ሁሉም የነዳጅ ተጠቃሚዎች በእኩል ሲስተናገዱበት የነበረ ነው።

መንግስት ለጥቅል ድጎማው በሚመድበው በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ምክንያት ለከፍተኛ ጫና ሲዳርግ ቆይቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከስድስት ወራት በፊት ባደረገው ስብሰባ ጥቅል የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱን በማስቀረት የታለመለት የነዳጅ ድጎማ እንዲተገበር ወስኗል።

ውሳኔውን ተከትሎ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለትም የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱን ለመተግበር የሚያሰችል ስምምነት ተደርጓል።

የታለመለት ድጎማ ስርዓቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለመተግበር የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኢትዮ ቴሌኮም  በኩል የለማ ሲሆን ቴክኖሎጂው በቀላሉ የነዳጅ ማደያዎችን ለመቆጣጠርና የነዳጅ  ድጎማ የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን  ለመለየት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

አሰራሩ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ የሚያገኙ ተጠቃሚዎችም ክፍያቸውን በቴሌ ብር እንዲፈፅሙ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ለዚሁ ትግበራ ያመች ዘንድ በሁሉም ክልሎች ያሉ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን የመለየትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ የማሰባሰብና አጠቃላይ ሂደት 85 በመቶ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ  እንዳሉት፤ ስርዓቱ መዘርጋቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረሰተብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚረዳ ነው።

በድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን መመዝገብና ማጣራት፣  የድጎማውን አተገባበር ስርዓት መዘርጋት፣ ተሽከርካሪዎቹ የድጎማ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጽ መለያ ስቲከር ማዘጋጀትና ለነዳጅ አቅራቢዎች ስለ ድጎማ ትግበራው የግንዛቤ  ማስጨበጫ  ተግባራት መከናወናቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማሪያም በበኩላቸው፣ የድጎማ ስርዓቱ  ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገበር ሲሆን በሂደት ሌሎችንም የሚያካትት ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚችል ገልጸዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ግዙፍ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር  ዘመናዊ አሰራርን እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት ያቀደው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሰራር እውን እንዲሆንም ኢትዮ ቴሌኮም በቴክኖሎጂው ረገድ ራሱን የቻለ መተግበሪያ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ተግባራዊ ማድረግም የቅንጦት ሳይሆን ሀገሪቱን በሁለንተናዊ ረገድ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከመጪው ሀምሌ 1 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም