ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ያሉትን ባህላዊ እሴቶች ለችግሮች እንደ መፍቻ ቁልፍ መጠቀም ይገባል

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ያሉትን ባህላዊ እሴቶች በተለያዩ ጊዜያት ለሚከሰቱ ችግሮች እንደ መፍቻ ቁልፍ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ያሉትን በርካታ ባህላዊ እሴቶች ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለመከባበርና እርስ በርስ ለመተጋገዝ ማዋል አስፈላጊ ስለመሆኑም ተገልጿል።   

ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ በመተሳሰብ አብረው የኖሩና አንዱ የሌላውን ባህል በማክበር ዘመናትን የዘለቀ ትስስር ያላቸው መሆኑ ይታወቃል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ሀደ ሲንቄ ገሪቤ ታፈሰ፤ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ታላቅ ቦታ የሚሰጠው "የሲንቄ" ባህላዊ እሴት ለሰላም ታላቅ ሥፍራ የሚሰጥ መሆኑን ይናገራሉ።

በባህላዊ እሴቱ መሰረትም ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሲወጡ የቆዩ እና አሁንም በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብም አቃፊነቱን በማስፋት ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተዋዶ በጋር እንዲኖር በባህላዊ ሥርዓቱ መሰረት አብሮ መኖር አለበት ብለዋል፡፡

የሰላም ጉዳይ በምንም የማይተካ ወሳኝ ነገር በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም ዘብ መሆን አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህም በሲንቄ ሥርዓት መሰረት በሕዝቡ ዘንድ ሰላም እንዲኖር እና አብሮ የመኖር እሴት እንዲጎለብት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክተርና ተመራማሪ ወይንሸት  ሀብተማሪያም፤ እንደ አገር ያሉንን ባህላዊ እሴቶች ለችግሮቻችን እንደ መፍቻ ቁልፍ ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የካበቱና የበርካታ ችግሮች መፍቻ የሆኑ እሴቶች እያሉ በአጠቃቀም ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይግባል ነው ያሉት።

በተለይም ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ለሰላምና አንድነት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር  ሰለሞን እምሩ፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ እየገጠማት ያለው አይነት ፈተና ገጥሟቸው የነበሩ በርካታ አገራት በጽናት ታግለው በማሸነፍ ታላቅ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም በዚሁ መንገድ እሴቶቿን በመጠቀም ከችግሮቿ ማለፍና ወደ ጀመረችው የእድገት ጎዳና ማምራት ይኖርባታል ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ካሉ በርካታ ባህላዊ እሴቶች መካከል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የሲንቄ ባህላዊ እሴት አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም