ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቆዳ፣ ባዮጋዝና ማዳበሪያ ምርት ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቆዳ፣ ባዮጋዝና ማዳበሪያ ምርት ከተሰማሩ ሁለት ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

የኮርፖሬሽኑ የኦፐሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ሰለሞን፤  ከፓርከር ክሌይ ኢትዮጵያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክብረአብ አበራ እና ከአክሼይ ጄይን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ስምምነት ካደረጉት ኩባንያዎች መካከል ፓርከር ክሌይ ኢትዮጵያ በቆዳ ውጤቶች ምርት በ30 ሚሊየን ብር በአዲስ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ1 ሺህ 150 ሜትር ስኩየር ሼድ ውስጥ ሥራ የሚጀምር ሲሆን ለ300 ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

ሁለተኛው አክሼይ ጄይን ደግሞ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ884 ሚሊየን ብር በ40 ሺህ ሜትር ስኩየር መሬት በባዮ ጋዝ እና ባዮ ጋዝ ማዳበሪያ ምርት ዘርፍ እንደሚሰማራ ተገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ የኦፐሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ሰለሞን፤ ኮርፖሬሽኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት እና በማስተዳደር ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሥራ እድሎችን በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት የበኩሉን ሚና በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለመሥራት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

የፓርከር ክሌይ ኢትዮጵያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክብረአብ አበራ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ባለፉት ዓመታት ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱን ገልጸው፤ አሁን በተሰጣቸው እድል ከዚህ በላይ ለማሳካት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የከአክሼይ ጄይን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሼይ ጄይን፤ ድርጅቱ የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር እና በታዳሽ ኃይል ላይ በስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ ላደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እየሰሩ ካሉ አምራቾች መካከል ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አምራቾች የውጭ ኩባንያዎች መሆናቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም