መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኑ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኑ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ነው
ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኑ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያስቀጥል መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ባሳለፍነው ሳምንት ባደረጉት ስብሰባ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን የፀጥታ ችግር መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፤ ጉባኤውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ፓርቲው ችግሩን በሰላም አማራጭ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ችግሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሕገ-መንግሥታዊ መርሆችን ባከበረ መልኩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በሰላም አማራጭ እንዲፈታ ፓርቲው መወሰኑን ነው ያነሱት፡፡
የፓርቲውን ውሳኔ ተከትሎም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት ቡድን በሰላም አማራጩ እንዲሳተፍና ሂደቱንም እንዲከታተል ተሰይሟል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መንግሥት ተገዶ ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት ጀምሮ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ አሰማኸኝ አስረስ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን አሸባሪው ሕወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ የክህደት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊቱ የትግራይ ክልልን ከተቆጣጠረ በኋላ በክልሉ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በተረጋጋ ሁኔታ የእርሻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ መንግሥት ሠራዊቱን ከመቀሌ ማስወጣቱንም አስታውሰዋል።
ሆኖም የሽብር ቡድኑ የመንግሥትን የሰላም እርምጃ ችላ በማለት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በኢትዮጵያ ላይ የህልውና አደጋ ከመደቀኑ በላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑን ወረራ በመቀልበስ ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ መንግሥት አሁንም በሰሜኑ ሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኑ የሚደነቅና ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ መክፈሏን ተናግረዋል።
በርካታ ሰዎችን ለሞት፣ ለአካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳትና መፈናቀል መዳረጉን ጠቅሰው፤ መንግሥት ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው የሰላም ጥረቶች ሰሚ ባያገኙም አሁንም ችግሩን በዘላቂነት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ዶክተር ቤተልሔም ላቀው፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እውን ለማድረግ ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም መንግሥት የወሰደው የሰላም አማራጭ ለኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ እና ዶክተር ስለሺ ኮሬ፤ መንግሥት የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት ያስቀመጠው አቅጣጫ ትክክለኛ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ከሰላም ኢትዮጵያና ሕዝቧ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ ለሰላም የሚከፈለው ዋጋ መከፈል አለበት ነው ያሉት።
ከዚህ አኳያ ችግሮች በሰላም አማራጭ እንዲፈቱ የምክር ቤቱ አባላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡም ነው የተናገሩት፡፡
አቶ አሰማኸኝ፤ በበኩላቸው በሰላም አማራጭ ሂደቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዮች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል።
አክለውም የሰላም ሂደቱ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት መከናወነ እንደሚገባው ጠቅሰው፤ በዚህ መሰረት ወደ ሰላም ውይይት ለሚመጣ አካል ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በሯ ክፍት ነው ብለዋል።