ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብቷ የላቀ ተጠቃሚ እንድትሆን መሰረት የሚጥሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

ሀዋሳ፤ ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ ) ኢትዮጵያ ከውሀ ሀብቷ የላቀ ተጠቃሚ እንድትሆን መሰረት የሚጥሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሀ አዱኛ ተናገሩ፡፡

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ የ15 ዓመታት መሪ የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት ማጠናቀቂያ መርሀ-ግብር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመረሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው፤  ሚኒስቴሩ በውሀ ሀብትና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ሁሉን አቀፍ ጥቅም እንድታገኝ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም አስቻይ የሆኑ የአዋጅ፣ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች የማሻሻል ስራ  መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ውሃንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ ድርሻ በሚያበረክቱበት መንገድ ለመምራት እንዲሁም ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ለማስፈን ነው፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከውሀ ሀብቷ የላቀ ተጠቃሚ እንድትሆን መሰረት መጣል የሚያስችል የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም ተፋሰሶች ላይ ለእያንዳንዳቸው የተለያዩ የዘላቂና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሠረት ያደረጉ የተፋሰስ ልማት ዕቅዶች እየተዘጋጁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያማከለ ውሀን የመንከባከብ ፣ የማበልፀግና የመቆጣጠር አሰራር እንዲኖርም ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እየተከናወነ ያለው የቅንጅት ስራ ከወሳኝ ተግባራት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ዕቅድ በርካታ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር አብርሀ፤ በትግበራ ምዕራፉም ሁሉም የየራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ በር የሚከፍት እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ደፈርሶ ፤ መሪ ዕቅዱ በውሀ ሀብትና አጠቃቀም ላይ ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታትንና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥን ዓላማ ያደረገ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውሃ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት መኖራቸውን የተናገሩት  አቶ ደበበ፤  ከዚህ በፊት በተናጥል የየራሳቸውን ዕቅድ አዘጋጅተው ሲተገብሩ እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም መሪ ዕቅዱ የሁሉም አካላት የጋራ ዓላማ ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ኃይልና አቅማቸውን  አስተባብረው በመጠቀም ትርጉም ያለው ሥራ እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ተቋማት ለየራሳቸው ዕቅድ ጥናትና ክትትል የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብም ረገድ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ዕቅዱ በአግባቡ ገቢራዊ በማድረግ  ለትውልድ የሚሸጋገር ዘላቂ የውሀ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዐት እንዲሰፍን ባለድርሻ አካላትን ወደ አንድ ማዕቀፍ አምጥቶ  የማስተባበር ኃላፊነቱን ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ዕቅዱ ላለፉት አራት ዓመታት ተፋሰሶቹ ያሉበት ነባራዊ ሁኔታና ተጋርጠውባቸው ያሉ ሥጋቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ላይ በማነጣጠር ሲዘጋጅ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስምጥ ሸለቆ ጥናትና ምርምር ማዕከል የባዮ ፊዚካል ክላስተር አስረተባባሪ ዶክተር ምህረት ዳናንቱ ናቸው።

በዋናነትም አባያ-ጫሞ ፣ ጨው ባህር ፣ ዝዋይ-ሻላ እና ሀዋሳ ንኡስ ተፋሰሶችን በመከፋፈል ጥልቀት ባለው ምልከታ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር  አስረድተዋል፡፡

በዚህም የሀይቆች ውሀ መጠን ማነስና ብክለት፣ የተፋሰሶች መራቆት፣ የወንዞች መበከልና የሀይቅ ዳርቻ ከሰዎች መኖሪያነት ነፃ አለመሆን፣ የውሀ ሀብት አጠቃቀምና ሌሎች ችግሮች መመላከታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዕቅዱ እንደየተፋሰሶቹና እንዳሉባቸው ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማመላከቱን ተናግረዋል።

ከ15 ዓመታት በኋላ ተፋሰሱ ድህንነቱ የተጠበቀ የውሃ ሀብትና ከግጭት መንስኤነት የፀዳ ዘላቂነት ያለው የአጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋትን እንደ ዋና ግብ ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ዕቅዱን ለመተግባርም  በ15 ዓመታት ውስጥ እስከ 70 ቢሊዮን ብር   እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፤ በዕቅድ ዝግጅቱ ወቅት አስተዋጽኦ  ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም