ቀጥታ፡

ሶስት ተቋማት የነዳጅ ድጎማን ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እና ኢትዮ ቴሌኮም ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ የተዘረጋውን አሰራር ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

መንግስት ለነዳጅ ተጠቃሚ የትራንስፖርት አገልገሎት የሚያደርገው ጥቅል ድጎማ በመንግስት በጀት ላይ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት በመዘርጋት አሰራሩን ለመተግበር ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለትም የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱን ለመተግበር የሚያሰችል ስምምነት ተደርጓል።

የታለመለት ድጎማ ስርዓቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለመተግበር የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኢትዮ ቴሌኮም  በኩል የለማ ሲሆን ቴክኖሎጂው በቀላሉ የነዳጅ ማደያዎችን ለመቆጣጠርና የነዳጅ  ድጎማ የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን  ለመለየት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

አሰራሩ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ የሚያገኙ ተጠቃሚዎችም ክፍያቸውን በቴሌ ብር እንዲፈፅሙ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በስምምነት ስነስርቱ ወቅት እንደተናገሩት፤  በሁሉም ክልሎች ያሉ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን የመለየትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሲያከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ የማሰባሰብና አጠቃላይ ሂደት 85 በመቶ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ግዙፍ ተቋማትን በቴክኖሎጂ የማስተሳሰርና  ዘመናዊ አሰራርን እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት ያቀደውን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሰራር እውን እንዲሆንም ኢትዮ ቴሌኮም በቴክኖሎጂው ረገድ ራሱን የቻለ መተግበረያ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከመጪው ሀምሌ 1 ጀምሮ ተግራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም