የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ ለምግብ አቅርቦትና ለጤናማ አኗኗር ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው- ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ ለምግብ አቅርቦትና ለጤናማ አኗኗር ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው- ዶክተር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ ለምግብ አቅርቦትና ለጤናማ አኗኗር ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በኢትዮጵያ አካል ጉዳት አገልግሎት (በገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ) ማዕከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለተከላ ከተዘጋጀው ችግኝ፤ ግማሽ ቢሊዮን የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች ናቸው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ ለምግብ አቅርቦትና ለጤናማ አኗኗር ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።
የምንተክላቸው ችግኞች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በመሆናቸው ከተፈጥሮ ሃብት ልማት ባለፈ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለችው መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በዛሬው እለት በሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በዘንድሮው ክረምት 20 ሺህ ችግኞችን የመትከል እቅድ እንዳላቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ ዘንድሮው ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችም ዝግጁ መሆናቸው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳት አገልግሎት የተዘጋጀው የወተት ላሞች እርባታ ፕሮጀክትም በዛሬው እለት በጤና ሚኒስትሯ ተመርቋል፡፡