ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በመንከባከብ ከብክነት በመታደግ በአግባቡ መጠቀም አለብን- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በመንከባከብ ከብክነት በመታደግ በአግባቡ መጠቀም አለብን" ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።

በውሃ፣ ምግብ እና ኢነርጂ ዋስትና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ጉባኤውን ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ የውሃ ማኔጅመንት ልህቀት ማዕከል እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ማዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤ ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ በኢትዮጵያ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ችግሮች ላይ በስፋት ለመነጋገር እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ያግዛል ብለዋል።

የውሃ ሃብት በዓለም ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠውና ብዙ ድካም የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በመንከባከብና ከብክነት በመታደግ በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጥበቃና የውሃ ልማት ለሌሎች አገሮችም የመጥቀም ዓላማ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህ አገራት እገዛና ትብብራቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።    

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ከተሞች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መኖሩንም ገልጸዋል፡፡

በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የግል ባለሃብቶች የከርሰ-ምድር ውሃ ለማውጣት የሚያደርጉትን ጥረት ያደነቁት ሚኒስትሩ፤ ሥራውን ማሳወቅና ሕጋዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሃብት ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር አሰፋ መኮንን፤ የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት ባግባቡ ለመጠቀም ከዝናብ ወቅት ባለፈ ለመስኖ እርሻ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡      

ለዚህም ስኬት የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን መሥራትና አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ግድቦችን በስፋት ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የውሃ ምህንድስና ከፍተኛ ባለሙያው ዶክተር ጥሩሰው አሰፋ፤ የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት ለመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ ተግባርን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጉባዔው የሚገኙ ግብዓቶች ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሥራ ክንውን እንዲሁም ለአገራዊ የፖሊሲ ግብአት አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የውሃ፣ ምግብና ኢነርጂ ዋስትና ጉባዔ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም