ቀጥታ፡

ወጣቶች የሀሰት ትርክትን በመናድ የሀገርን ብልፅግና እንዲያረጋግጡ ተጠየቀ

ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቶች የሀሰት ትርክትን በመናድና የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ግንብን በመገንባት የሀገርን ብልፅግና ሊያረጋግጡ እንደሚገባ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ካሳሁን እምቢአለ ተናገሩ።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ  የ2014/15 የበጎ ፈቃድ የአርጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን እያካሄደ ነው።

የከተማው ተቀዳሚ  ምክትል ከንቲባ በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ  ወጣቶች ለሀገር ሁለንተናዊና ዘላቂ ግንባታ ያላቸውን የማይተካ ሚና በተደራጀ አግባብ ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

''ሀገርን ለማስቀጠል ወጣቶች የሀሰት ትርክትን በመናድ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ግንብን በመገንባት የሀገራቸውን ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ሊያረጋግጡ ይገባል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር  አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን  ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሥራን እያከናወነች ነው።

ወጣቶችም የአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

''የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት የሚያስከትላቸው ተጽኖዎችና መፍትሄዎቻቸው'' በሚል ጥናታዊ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

 በአሁኑ ሰዓትም የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር መካሄድ ጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ሲሆን ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በተጨማሪ ደም ልገሳና ሞዴል የከተማ ግብርና ሥራዎችን መጎብኘት የመርሐ ግብሩ አካል መሆናቸውም ተመላክቷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ዓለሙ ስሜን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም