ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው - አፈ - ጉባኤዋ

ጎባ ሰኔ 27/2014(ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በመመለስ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ገለጹ።

አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ ከክልሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በምስራቅ ባሌ ዞን ጎሎልቻና ጊኒር ወረዳዎች  የተገነቡ የልማት ፕሮጄክቶችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ከተመረቁት የልማት ፕሮጄክቶች መካከል በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጎሎልቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይገኝበታል።

ሌላው በአፈ ጉባኤዋ ለምረቃ ከበቁት ፕሮጄክቶች መካከል በጊኒር ወረዳ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የካራ አዳኖ የኢፈ ቦሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚገኝበት ተመልክቷል፡፡

ትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጻህፍትና ሌሎች ለትምህርት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን ከ500 የሚበልጡ ተማሪዎችንም ተቀብሎ የማስተማር አቅም እንዳለው ተገልጾዋል፡፡

የጎሎልቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የቀዶ ህክምና፣ የማዋለጃ፣ የህጻናትና ተመላላሽ የህክምና አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችም ተመርቀው ለአገልግሎት ከበቁ ፕሮጀክቶች መካከል መሆናቸው ተመልክቷል።

ሆስፒታሉ የጎሎልቻ ወረዳ ነዋሪዎች የተሻለ የህክምና አገልግሎት በአካባቢያቸው እንዲያገኙ  እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ በወቅቱ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በመመለስ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።

በዚህም ህዝቡ በተደጋጋሚ ያነሳ የነበረውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በመለየት በአጭርና ረዥም ጊዜ ዕቅድ ደረጃ በደረጃ በመመለስ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በትምርትና ጤና ላይ ያተኮሩ የመሰረተ ልማቶች የማበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በተጓዳኝ አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ እንደሆነ ነው ወይዘሮ ሰዓዳ የተናሩት፡፡

አፈ-ጉባኤዋ እንዳሉት የክልሉ መንግስት የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እያደረገ የሚገኘው ጥረት እንዲሰምር የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን በመጠበቅ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ በቀለ በበኩላቸው፤ ሀገሪቷ  ያጋጠሟትን ተግዳሮቶችን ተቋቁማ ለህዝብ ዕድገትና ተጠቃሚነት ወሳኝ የሆኑ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተሰርተው ለአገልግሎት እየበቁ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይ የክልሉ መንግስት የምሥራቅ ባሌ ዞንን የቱሪዝምና የግብርና እምቅ አቅም በመረዳት ለመንገድ፣ ትምህርትና የጤና መሰረተ ልማት የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ህዝቡም ፕሮጀክቶችን በመንከባከብ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጥ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከጎሎልቻ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ከድር በሰጡት አስተያየት በተለይ የሆስፒታሉ መገንባት የተሻለ ህክምና በአካባቢያቸው በማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡

የጊኒር ወረዳ ነዋሪው አቶ መሀመድ ሃሺም በበኩላቸው "በአካባቢያችን የተገነባውን ትምህርት ቤት በአግባቡ በመያዝ ልጆቻችን አስተምረንበት ለቁምነገር በማብቃት ድርሻችንን እንወጣለን" ነው ያሉት፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከሰኔ 20 እስከ  ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው  ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት የማብቃቱ  ሥነ-ሥርዓት  እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም