ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩን በደብረ ብርሃን ከተማ ጀመረ

ሰኔ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ የ2014/15 ዓ.ም በጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩን በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ጀምሯል።

''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' የሚል ስያሜ ያለው መርሃ ግብር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፣የደም ልገሳና ሞዴል የከተማ ግብርና ሥራዎችን መጎብኘትን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ዓለሙ ስሜን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ አባቶቻችን ነጻነቷ ሳይደፈር ያስረከቡንን አገር ወጣቱ ዘመኑ በሚጠይቀው መስዋዕትነት አገሩን በመተባበር ሊጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊና ዘላቂ ግንባታ ያላቸውን ሚና መወጣት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ለማስቀጠል ወጣቶች የሀሰት ትርክትን በመናድ የሰላም፣የፍቅርና የአንድነት ግንብን በመገንባት የአገራቸውን ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ሊያረጋግጡ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአየር መዛባትን ለመከላከል የአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በመተግበር ላይ ነች ብለዋል።

መርሃ ግብሩ በቀጠናው ባሉ አገራት እንዲስፋፋ መደረጉ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

ወጣቶችም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲደርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ከመርሃ ግብሩ በተጨማሪ አረንጓዴ አሻራ የተመለከተ ውይይት ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም