ቀጥታ፡

ጥላቻን በመተው ዘመኑን በይቅርታ ለማሳለፍ እንደሚጥሩ በሀዋሳ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሀዋሳ መስከረም 2/2011 በተጀመረው አዲስ ዓመት ጥላቻን  በመተው በይቅርታ ፣ በፍቅርና  በአዲስ ተስፋ  ለማሳለፍ እንደሚጥሩ  በሀዋሳ ከተማ  ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት  ካለፈው ዓመት ችግር በመማር  በ2011 ዓመተ ምህረት  አዲስ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ቆንጅት ደሳለኝ በሰጡት አስተያየት 2010 ዓመተ ምህረት የተለያዩ ፈተናዎችን ማስተናገዳቸውና ሲያስቡትም  ምቾት እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በአካባቢዎች ተፈጥሮ በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ከነቤተሰባቸው ተፈናቅለውና ታስረው እንደቆዩም አመልክተዋል፡፡ " ለኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙሃን ኢትዮጵየያዊያን አስጨናቂ ወቅት የነበረ ቢሆንም በከፊልም ቢሆን ደግሞ ጥሩ ጅማሮዎችንም ያየሁበት ነው" ብለዋል፡፡ አዲሱ ዓመት መልካም ዘመን እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት ወይዘሮ ቆንጂት ተፈናቅለው በየቦታው ያሉ ወገኖቻችን ማረፊያ አግኝተው ሰላማዊ  ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ምኞታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ቂምና በቀልን አስወግዶ በይቅርታ  በማሳለፍ ዘመኑ መልካምነት እንዲበዛ እንደሚመኙ ጠቁመው በደል ያደረሱባቸው ሰዎች ከልብ ይቅርታ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ  አፀደ ገብረመድህን በበኩለቸው ያለፈው ዓመት "የኢትዮጵያ ህዝቦች አዲስ ተስፋ የሰነቁበት ፣ አንድነትና ሰላም በተመለከተ ደግሞ አብዛኛኖቻችን በስጋት ተውጠን የከረምንበት ዓመት ነበር" ብለዋል፡፡ ሆኖም አሁን የሚታዩ ለውጦች ተስፋ የሚሰጡ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ያለፈው ዓመት አዳዲስ ነገሮችን ማየት የተቻለበትና በዚያው ልክ ደግሞ ችግር እንደነበር በማስታወስ አስተያየቱን የሰጠው ደግሞ  ወጣት ክብሩ ዮሐንስ ነው፡፡ በተጀመረው አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያዊነት በማሰብ  ፍሬያማ ለመሆን  መስራትና  ይቅርታን የምንተግብርበት ዓመት መሆን አለበት ብሏል  ወጣት ክብሩ፡፡ አቶ ዓለማየሁ አበበ  የተባሉት የሀዋሳ ነዋሪ በበኩላቸው ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያዊያንን ባህል፣ እሴትና ወግ የማይወክሉ ችግሮች የታዩበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ  የብሄር ግጭቶችም በየቦታው ተስተናግደው ማለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡ " በማወቅም ሆነ ባለማወቅም አንድኛችን ሌላኛውን ጎድተናል ፤ የተጎዳዳን ህዝብ ስለሆንን እኔ ወደ 2011 የሚሸጋገረው ይቅርታ በማድረግና በመጠየቅ ነው"ብለዋል፡፡ " ለፍቅር ትልቅ ቦታ ሰጥተን ተዋድደን አብረን መኖር አለብን " ያሉት አቶ አለማየሁ የሚከናወኑ ተግባራት ለሃገር የሚጠቅሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ " የሃሳብ ፍጭት በማድረግ ፋንታ ስሜታዊ በመሆናችን የከፈልነው ዋጋ ብዙ ስለሆነ ካለፈው 2010 ጥፋቶቻችን በመማር ምክንያታዊ መሆን ያስፈልገናል " ያለው ደግሞ ወጣት አዳነ ዎቲ ነው፡፡ ዘመኑ ጥላቻን  በመተው በኃላፊነት መንፈስ  ይቅርታ በማድረግ በፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም