በትምህርት የታነጸ ትውልድን ለማፍራት ለትምህርት ተቋማት ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው

63

ጅማ፣ ሰኔ 26/2014 (ኢዜአ) በትምህርት የታነጸ ትውልድን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ወሳኝ ለሆነው የትምህርት ተቋማት ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ገለጹ ፡፡

በጅማ ዞን ኦሞናዳ ወረዳ በጨፌ ነጋ ቀበሌ 38 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት የተገነባ የኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት ትላንት ተመርቋል፡፡

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በወቅቱ እንዳሉት ትምህርት ትውልድን በእውቀት በማነጽ ሀገርን ከድህነት የሚያወጣ ሃይል የምናፈራበት ወሳኝ የልማት ዘርፍ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

"የበለጸጉ ሀገራት አስተማማኝ የኢኮኖሚ አቅም በመገንባት ለሌሎች ሀገራት መትረፍ የቻሉት የተማረና የነቃ የሰው ሃይልን በብዛት በማፍራታቸው በመሆኑ እኛም ህዝባችንን በትምህርት ማንቃት አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሀገራችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች እየተፈተነች ቢሆንም ፈተናውን ተቋቁማ ለእድገት ወሳኝና ትላልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ተሰርተው ለአገልግሎት እየበቁ ይገኛሉ" ብለዋል።

በጅማ ዞን ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ወጪ 229 የሚሆኑ የትምህርት፣ የመንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና፣ የመስኖ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

የጅማ ዞን የትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አነዋር አባ ጊዲ በበኩላቸው በወረዳው ጨፌ ነጋ ቀበሌ የተገነባው ኢፋ ቦሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥና ውጤታማ የሰው ሃይል ለማፍራት ያስችላል ብለዋል፡፡

በእለቱ በናዳ ከተማ በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የወረዳ የጤና ጽህፈት ቤት ቢሮ ግንባታው ተጠናቆ ለምርቃት በቅቷል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ናስር ራያ እንዳሉት በወረዳው በ94 ሚሊየን ብር ወጪ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጤና ኬላዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመጠጥ፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ የ16 ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ልጆቻቸው በአቅራቢያቸው ጥራት ያለው ትምህርት  እንዲማሩ የሚያስችል ትምህርት ቤትን ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃቱ መደሰታቸውን የተናገሩት የኦሞናዳ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዛኪር አባ ቡልጉ ናቸው።

በቀጣይም የመብራት፣ የመንገድና የትራንስፖርት ችግሮቻቸውን መንግስት እንዲቀርፍላቸው ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ከዲጃ መሀመድ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱን በአግባቡ ይዞ ልጆችን አስተምሮ ለቁምነገር ማብቃት የኛ ድርሻ ነው ብለዋል።

መንግስት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት በአከባቢያቸው በመስራቱ መደሰታቸውን ገልጸው የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች  እንዲማሉላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም