ዛሬ በምንተክላቸው ችግኞች የተሻለና ምቹ ሀገር ለተተኪ ትውልድ እንፈጥራለን- ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

75

ሰኔ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)''ዛሬ በምንተክላቸው ችግኞች የተሻለና ምቹ ሀገር ለተተኪ ትውልድ እንፈጥራለን'' ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ክልሉ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በኢሉባቦር ዞን ያዮ ወረዳ አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በመጪዎቹ አስር ዓመታት በክልሉ ያለውን የደን ሽፋን 34 በመቶ ለማድረስ ይሰራል።

May be an image of 5 people, people standing and outdoors

ይህንንም ለማሳካት ዛሬ በይፋ በተጀመረው 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ችግኞችን በክልሉ አቅም ብቻ ለመከትል ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

"ችግኞችን ስንተክል ደግሞ ድርብ ግቦችን ለማሳካት አልመን በመሆኑ ኢኮኖሚያችንን ይበልጥ ሊያግዙ የሚችሉ ጥምር ስራዎችንም ከችግኝ መትከል ስራው ጎን ለጎን ማስኬድ ይኖርብናል" ብለዋል።

የቡና፣ የአቮካዶና የማር ኢንሼቲቮች ችግኞችን ከመትከል ጋር ተጣምረው በልማቱ ውስጥ ትኩረት የምንሰጣቸዉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸዉ ተግባራት ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

"ዛሬ በምንተክላቸዉ ችግኞች ነገአችንን እየሰራን ለተተኪ ትውልድም ምቹ ሀገርን የመፍጠር ስራ እየሰራን ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ሁሉም ዜጋ ሀገርን የመገንባት አካል በሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩሉን ማበርከት ይጠበቅበታል ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከሚሰራው የደን ልማት አርሶ አደሮች በቀጥታ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት አዋጅ ይዘጋጃል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ በበኩላቸው " በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ አካባቢ ቢኖረንም በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ችግሮች ለአደጋ በመጋለጡ ይህን መልሶ የመስራት ኃላፊነት ወድቆብናል" ብለዋል።

አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠርና ምቹ ሀገር መፍጠር ዓላማው ባደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም "የኢኮ-ቱሪዝምን፣የደን ፓርክ ማቋቋምን፣እንዲሁም የአግሮ ፎረስትሪ ግቦችን ለማሳካት ይሰራል" ብለዋል።

በሳይንሳዊ መንገድ መትከልና ወጥና ቀጣይነት ያለው እንክብካቤ ማድረግ፣በተፋሰስ ልማት ስራዉ የተከናወነውን ችግኝ ተከላ ሙሉ ማድረግና ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም አቶ አበራ አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ የሚተከሉትን ችግኞች በመንከባከብና በመጠበቅ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነታቸዉን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ በያዮ ወረዳ የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።

አቶ መሐመድሳሊ አብዱ የያዮ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ በዩኔስኮ ተመዝግቦ የሚገኘው የያዮ ጥብቅ ደን ቀድሞውኑ በኅብረተሰቡ ጥበቃ ሲደረግለት የኖረና አሁንም እየተጠበቀ የሚገኝ ስለመሆኑ ይገልፃሉ።

ኅብረተሰቡ ደንን ለማንኛዉም ግልጋሎት ሲጠቀም አስቀድሞ ችግኞችን በመትከል የመተካት ባህሉ የዳበረ መሆኑንም አቶ መሐመድሳሊ አክለው ገልጸዋል።

አቶ ተሰማ ከበደ በበኩላቸው በአሁን ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተተከሉ የሚገኙ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች መትከል ብቻ ሳይሆን የመንከባከብና ለተፈለገዉ ዓላማ የማብቃት ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።

"ችግኝ እንደስሙ ብዙ ክትትል ያስፈልገዋል" ያሉት አቶ ተሰማ፤ ይህንን ኃላፊነት ደግሞ በተከላዉ ባሳየነዉ አንድነት በመንከባከብ ስራውም ማሳየት አለብን ብለዋል።

በዩኔስኮ ተመዝግቦ የሚገኘዉ የያዮ ጥብቅ ደን በ167 ሺህ 21 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም