የአፍሪካ ልማት ባንክ የአፍሪካን የምግብ ምርት ለማሳደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ አሜሪካ ገለጸች

321

ሰኔ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአፍሪካ ልማት ባንክ አፍሪካ በምግብ እራሷን እንድትችል የምግብ ምርቷን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ አሜሪካ ገለጸች።

ባንኩ በአፍሪካ የሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አነስተኛ ግብርና አምራቾች የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችሉ ስንዴ፣በቆሎ፣አኩሪ አተር እና ሌሎች ዋና ዋና የሰብል ዘሮችን ማምረት እንዲችሉ እንዲሁም ለማዳበሪያና ለግብርና ስራዎች አገልግሎት ይውል ዘንድ በግንቦት ወር 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

ይህም አፍሪካ ለቀጣዮቹ አራት የምርት ወቅቶች ወደ 12 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ 38 ሚሊዮን ቶን የምግብ እህል ምርቶችን በፍጥነት እንድታመርት ያስችላታል ተብሏል፡፡

በተለይም በሩሲያ እና ዩክሬን ግጭት ምክንያት በአህጉሪቱ ላይ እያንዣበበ ያለውን የምግብ ቀውስ ለመከላከል ባንኩ የምግብ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

በቡድን 7 አባል አገራት ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን እና ሌሎች የቡድን 7 ሀገራት መሪዎች የአለም አቀፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።

May be an image of 7 people and people standing

ከዚህም ውስጥ አሜሪካ ሀምሳ በመቶ ያህሉን እንደምትሸፍን አስታውቀዋል፡፡

የባይደን አስተዳደር ድጋፉ በሚስፈልጋቸው ሀገራት በከፍተኛ የምግብ እጥረት፤ በነዳጅ እና በጦርነት ምክኒያት የሚደርሰውን የማዳበሪያ ዋጋ ንረት ለመቋቋም ይውል ዘንድ ከሚደረገው አጠቃላይ ድጋፍ ውስጥ 760 ሚሊዮን ዶላር ያህሉን አገራቸው ትመድባለች ነው ያሉት።

አሜሪካ እንደ ድርቅ ወይም ጎርፍ ባሉ አስከፊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ምክንያት የሚከሰተውን ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ለመከላከል የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጣውን የአፍሪካ አደጋ ስጋት ፋይናንስ የተሰኘውን ፕሮግራም እንደምትደግፍም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በ2018 ያስጀመረው ይህ ፕሮግራም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ የሚያግዝ ሲሆን በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አኪንዉሚ አዴሲና ፤ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ሌሎች የቡድን 7 ሀገራት የባንኩን ስራ በተጨባጭ ለመደገፍ እንዲሁም የአለም የምግብ ዋስትናን ለመፍታት ያደረጉትን ጉልህ አስተዋፅዖ አድንቀዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት ለአለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ተግዳሮቶች ባለብዙ ዘርፍ ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ የልማት ፕሮግራሞች ይገኙበታል ብለዋል የባንኩ ፕሬዝዳንት፡፡

ድጋፉ የተደረገው አፍሪካ ከፍተኛ እገዛ በሚያስፈልጋት ወቅት በመሆኑ ባንኩና ሌሎች ተቋማት ለሚያደርጉት ጥረት ተጨማሪ ጉልበትን ይሰጣል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚመጡ የእህል ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኗን የገለጹት የባንኩ ፕሬዝዳንት በጦርነቱ ምክንያት በስንዴ፣በቆሎ፣አኩሪ አተር እንዲሁም ሌሎች ከሁለቱ ሀገራት በዋናነት ወደ አፍሪካ በሚላኩ ሰብሎች ምክኒያት አህጉሪቱ ወደ 30 ሚሊዮን ቶን የሚሆን የምግብ እጥረት ሊያጋጥማት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ባይደን በሩሲያ እና ዩንክሬን ጦርነት ምክንያት እየተባባሰ የመጣው የምግብ እጥረት የሚያስከትለውን ተፅኖ ለመቅረፍ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት 2 ነጥብ 76 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አሜሪካ እንደምታደርግ ገልጸው ይህም አርባ ሰባት የአፍሪካ ሀገራትን እና የምግብ እጥረት ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም