በወላይታ ዞን የገጠር መንገዶችና የድልድይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ

128

ሶዶ ሰኔ 26/2014 (ኢዜአ) .... በወላይታ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የገጠር መንገዶችና የድልድይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ።

መንገዶቹን መርቀው የከፈቱት የደቡብ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ፤ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ለገጠር ተደራሽ መንገዶች ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ 105 የገጠር ተደራሽ የመንገድ ፕሮጀክቶች በ90 ቀናት እቅድ ለማጠናቀቅ መጀመራቸውን ጠቅሰው ከእነዚህ 26 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አክለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ በወላይታ ዞን ለአገልግሎት የበቁት 11 የገጠር ተደራሽ መንገድና 2 ድልድዮችንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዚህ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተሰራው ስራም አበረታች ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።

አያይዘውም ከፕሮጀክቶች መጓተት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ በጊዜና በገንዘብ ተገድበው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ለመንገድና ድልድይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰቡት ዶክተር አበባየሁ፤ በተለይም ደለሎችን በማንሳትና የተፋሰስ ስራዎች በማጠናከር እንደዚሁም ዛፎችን በመትከል እንዲንከባከብ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው መንገድ የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ገልፀው ዛሬ በዞኑ ከ103 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ህዝቡ ያለውን ሀብት እንዲያንቀሳቅስና እንዲገለገል መንገድ መሠረታዊ ግልጋሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው በተለይ የገጠር መንገዶችን ከወረዳ ጋር በማገናኘት ስራው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአገልግሎት ከበቁት ድልድዮች አንደኛው የወላይታና የሀዲያን ዞን የሚያገናኝ መሆኑም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አክለዋል።

በዞኑ የድጉና ፋንጎ ወረዳ ቀርጨጬ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ተስፋነሽ ኤቢሶ ድልድዩ ከመሰራቱ በፊት በተለይ በክረምት ወቅት በሰውና በንብረት ላይ አደጋዎች ሲደርሱ እንደነበር ተናግረዋል።

ድልድዩ መሰራቱ በወንዙ መሙላት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን የሚቀንስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በወረዳው የሆለታ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃነሽ ኤና በበኩላቸው የቀርጨጬ መንገድ ለተሽከርካሪም ሆነ ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች የማይመች እንደነበር ተናግረዋል።

በዚህም "የሰው ህይወት ላይ በተለይም ነፍሰጡሮችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ አስቸጋሪ በመሆኑ በርካታ ችግሮች ስናስተናግድ ቆይተናል" ብለዋል

የመንገዱ መሰራት ለተለያዩ የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ የሚሰጣቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም