የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የክልሉን አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስጀመሩ

62

ሰኔ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ‘‘አረንጓዴ አሻራችን ለትውልዳችን’’ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን የክልሉን አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጋምቤላ ወረዳ ቀርሚ ቀበሌ አስጀመሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ በአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

ዕቅዱን እውን ለማድረግ አመራሩ መላውን የክልሉን ነዋሪ በማስተባበር ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

May be an image of 11 people, people standing and grass

ባለፉት ሶስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በተሰራው ስራ በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎችን በእጽዋት ማልበስ መቻሉን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ካለፈው መልካም ተሞክሮ በመውሰድ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ እስከ መስከረም አጋማሽ በሚዘልቀው የችግኝ ተከላ ሁሉም ሰው ቢያንስ 100 ችግኝ በመትከል ለዕቅዱ መሳካት የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተራቁቶ የነበረ ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ወደ ቀድሞ ይዘቱ መመለሱን ተናግረዋል።

በዘንድሮ መርሃ ግብር የአካባቢውን ስነ-ምህዳር በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጂት በመርሃ ግብሩ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ተማሪዎች በስፋት እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

የአኝዋሃ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኡቦንግ ኡጁሉ በበኩላቸው የሽብር ቡድኖችን እኩይ ሴራ በመመከት የተጀመውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስኬታማ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በክልሉ ዘንድሮ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የፍራፍሬና የደን ጥምር እርሻ ችግኞች እንደሆኑ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም