ቀጥታ፡

ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ከመተናኮስ ወጥተው ሰላማዊ መንገድን ቢከተሉ ይሻላቸዋል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ወልዲያ፣ ሰኔ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠላቶቻችን ያለፈውን ኪሳራቸውን ተገንዝበው ኢትዮጵያን ከመተናኮስ ወጥተው ሰላማዊ መንገድን ቢከተሉ ይሻላቸዋል ሲሉ የኢፌድሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስገነዘቡ፡፡

በዘመቻ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ጀብዱ ለፈጸሙ 8ኛ ዕዝ አባላትና ክፍሎች የሜዳሊያ ሽልማት የማበርከት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት እየተሸነፈ አሸንፌአለሁ፤ እየሸሸ መክቻለሁ በማለት የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን በሀሰት ትርክት እያደናገረ ነው።

ቡድኑ ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበርና የጥፋት ተልዕኮ በማንገብ የሚያደርገውን የውክልና ጦርነት መላው ኢትዮጵያዊ ተገንዝቦ ሊያከሽፈው እንደሚገባ ገልጸዋል።

8ኛ ዕዝ ቡድኑን ለመደምሰስ በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት የጀግንነት ገድል ማሳየቱን አስታውሰው፤ በወቅቱ ሀገር ተደቅኖባት ከነበረው የመፍረስ አደጋ የታደገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ጠላቶቻችን ያለፈውን ኪሳራቸውን ተገንዝበው ኢትዮጵያን ከመተናኮል ካልወጡ የተለመደው ቅጣት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።

የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው፤ የሚሌን መስመር ለመቁረጥ ቋምጦ የነበረውን አሸባሪው ህወሃት ጀግናው 8ኛ ዕዝ ከሌሎች አቻዎቹ ጋር በመሆን ተገቢውን ቅጣት እንደቀጣው ገልጸዋል።

በዚህም ሀገርን ያኮራ ሰራዊት እንደሆነ ተናግረዋል።

በባቲ፣ በቡርቃ፣ በካሳጊታ፣ በጭፍራና በዞብል ሰንሰለታማ ተራራዎች ጠላትን እጅ በእጅ ተዋግተው የህዝብ አለኝታና ለሀገር መከታ የሆኑ ጀግኖች ዛሬ የጀግና ሜዳሊያ ለመሸለም መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ዕዙ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ አኩሪ ገድል መፈጸሙን ጠቅሰው፤ ዕዙ በተገኘው ድል ሳይዘናጋ ለላቀ ግዳጅ የበለጠ ዝግጁ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ከሰራዊቱ ሳይለዩ ስንቅ በማቀበል፣ ቁስለኛ በማግለልና በመዋጋትም ጭምር ትልቅ አስተዋጥኦ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ 8ኛ ዕዝ ጠላትን ለመመከትና ለመደምሰስ በአፋር በረሃማ ቦታዎች ያደረገው ገድል በታሪክ የማይረሳ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጠላት በቀመሰው ቅጣት ትምህርት ካልወሰደና ትንኮሳ ከፈጸመ የለመደውን ቅጣት ያገኛል ብለዋል።

ለዚህም በቂ ዝግጁነት እንዳለ ጠቁመዋል።

በዕለቱ ለ3ኛ ደረጃ ሜዳይ ምርጥ አዛዦች፣ ለ3ኛ ደረጃ ምርጥ ተዋጊዎችና ድጋፍ ሰጪዎች እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ሜዳይ፣ ለምርጥ አዛዥ፣ ለምርጥ ተዋጊ፣ ለምርጥ ድጋፍ ሰጪና ሌሎችም አስተዋጽኦ የነበራቸው ተሸልመዋል፡፡

ተሸላሚዎች የተበረከተላቸው ሽልማት አብረዋቸው የተዋደቁ ጓዶቻቸው ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል።

ሽልማቱ ለላቀ ግዳጅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረው፤ ህዝብና ሀገርን ከጠላት የመጠበቅ ግዴታቸውን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም