ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች እንዲወገዱ ዘርፉ የተሻለ የህግ ማእቀፍ ያስፈልገዋል

ሀዋሳ፣ ሰኔ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች እንዲወገዱ ዘርፉ የተሻለ የህግ ማእቀፍ እንደሚያስፈልገው የጤና ሚኒስትራ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ሚኒስትሯ ከጤና ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት የሀዋሳ ቅርንጫፍን የስራ እንቅስቃሴ ዛሬ ጎብኝተዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት የሀዋሳ ቅርንጫፍ ብቻ በግዥ፣በመንግሥትና በአጋር አካላት በነጻ የሚቀርቡ መድኃኒቶችንና መገልገያ መሳሪያዎችን በማሰራጨት ከ500 በላይ ጤና ተቋማትን እንደሚያስተዳደር ገልጸዋል።

ሀዋሳን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የመድሀኒት አቅራቢ ቅርንጫፎች አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ያደረጓቸው የተቀናጀ የካይዘንና የጥራት ማሻሻያ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰው አሁንም በሪፎርም ደረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ፣ የግዥ ሥርዐቱ የተሻለ እንዲሆን የማድረግ ስራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የህግ ማእቀፎችን ማሻሻል ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ የመድኃኒት ግዥ እና ሌሎች ማናቸውም እቃዎች የሚገዙበት ተመሳሳይ ህግ መኖሩ በጤና ሴክተሩ ላይ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብድቃድር ገልገሎ የአገልግሎቱ ዋና አላማ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህበረተሰቡ ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን ለማስፈጸም ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አንጻር ውስንነቶች እንዳሉበት ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

ከውስንነቶቹ መካከል የሰው ሃይል አስተዳደር፣በፋይናንስና ግዥ ሥርዐቱ ጋር ተያይዞ ውስብስብ የሆኑ ማነቆዎች እንዳሉ አውስተዋል።

እነዚህ ማነቆዎች እንዲፈቱ ለመንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቶ በዚህ ዓመት ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ አገልግሎቱ በሁለት መንገድ መድኃኒት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ ያመላከቱት ዶክተር አብድቃድር 70 በመቶ የሚሆነው እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ወባ፣ኤች አይቪ እና የቤተሰብ ምጣኔ የመሳሰሉት መድኃኒቶችን በነፃ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል።

ቀሪው ደግሞ ከአንድ ጤና ተቋም ከሚቀርበው የመድኃኒት ፍላጎትና ጥያቄ መሠረት በማድረግ ከውጭ ሀገር በግዥ እንደሚሰራጭ አመላክተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው በአገልግሎቱ፣በአዳማ እና ሀዋሳ ቅርንጫፎች ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊነትን የተላበሰ በመሆኑ ለሌሎች ተምሳሌት ያደርጋቸዋል።

በተለይ የሀዋሳ ቅርንጫፉ በስትራቴጂ እየተመራ በከተማ ግብርና ሞዴል ለመሆን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴና ተሞክሮ በሌሎችም የመንግስት ተቋማት ሊስፋፋ እንደሚገባው አፅንዖት ሰጥተውታል።

የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለቆመለት አላማ ምላሽ ሰጪ እንዲሆን ቋሚ ኮሚቴው አባላት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም