ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የፖለቲካ ምህዳር አቅጣጫ የሚቀይር ፕሮጀክት ነው-ኡስታዝ ጀማል በሽር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የፖለቲካ ምህዳር አቅጣጫ የሚቀይር ፕሮጀክት ነው-ኡስታዝ ጀማል በሽር

ሰኔ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የፖለቲካ ምህዳር አቅጣጫ የሚቀይር ፕሮጀክት ነው” ሲል “የአባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤትና የሕዳሴ ግድብ ተሟጋች ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጸ።
ኢትዮጵያውያን “እኛ የአባይ ንጉሶች ነን” በሚል መነሳትና መስራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለተቋሙ ጋዜጠኞች በአዳማ ከተማ ሙያዊ ስልጠና እየሰጠ ነው።
“የአባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤትና የሕዳሴ ግድብ ተሟጋች ኡስታዝ ጀማል በሽር በስልጠናው ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና አገራዊ አንድነትን አስመልክቶ እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች ዙሪያ ገለጻ አድርጓል።
የሕዳሴ ግድብ ከጅማሮው አንስቶ የማጠልሸትና የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጿል።
በግድቡ ዙሪያ የሚሰራጩ የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻዎች ለመመከት እሱና የስራ አጋሮቹ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ሙግት በማድረግና እውነታውን የማስረዳት ስራ እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግሯል።
“ግብጾች የአባይ ልጆች ነን ብለው ሰፊ ስራና ቅስቀሳ እንደሰሩ ሁሉ እኛም የአባይ ንጉሶች ነን ብለን እየሰራን ነው” ብሏል ኡስታዝ ጀማል።
የ”አባይ ንጉሶች” ሚዲያ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ ባለቤትነትና የግድቡ ግንባታ አስመልክቶ ለዓለም አቀፉ ማህበሰብ የማስገንዘብ ስራ እያከናወነ ነው ብሏል።
መገናኛ ብዙሃንና የሚዲያ ባለሙያዎች ግድቡን አስመልክቶ በተለያዩ ቋንቋዎች የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብትና ባለቤትነት እንዲገነዘብ የማድረግ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸው አመልክቷል።
በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሊኖር የሚችለውን የግንዛቤ ክፍተቶች የማጥበብና በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ የኛ ድርሻ ነው ሲል ገልጿል።
በተለያዩ ቋንቋዎች በሚከናወኑ የኮምዩኒኬሽን ስራዎች “የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት በሌሎች ልንቀማ ነው የሚል ስግብግባዊ አካሄድ በአግባቡ ተረድተን ችግሮችን መጋፈጥና ማሸነፍ እንችላለን” ነው ያለው “የአባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤት።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የፖለቲካ ምህዳር አቅጣጫ የሚቀይር ፕሮጀክት ነው” የሕዳሴ ግድብ ተሟጋቹ የኢትዮጵያዊን የኑሮ ሂደት ከመሰረቱ ይለውጣልም ብሏል።
“የውጭ ኃይሎች ፍላጎታቸውን ለመጫን እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ የሚያስቆምና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ እንድትይዝ ያደርጋታል” ሲል ገልጿል።
“የአባይን ልጅ ከእንግዲህ ውሃ ሊጠማው አይገባም ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውሃ ልታጠጣ ይገባል ብለን ልክ እነሱ የአባይ ልጆች ነን እንደሚሉት እኛ የአባይ ንጉሶች ነን ብለን መነሳትና በትብብር መስራት ከኛ ይጠበቃል” ብሏል።
“እኛን በኛው ለማባላት ነጻ አውጪ ነኝ ስልጣን መያዝ አለብኝ” ብለው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በፋይናንስና በቁሳቁስ በመደገፍ “በኛው እኛው ላይ” እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።
“የተሳፈርንባት ብቸኛዋ መርከብ ኢትዮጵያ ናት” ያለው ኡስታዝ ጀማል ይሄን በመረዳት ኢትዮጵያን ሊያጠቃ የመጣ ማንኛውንም አካል በጋራ መመከት ይገባል ብሏል።ኢትዮጵያን ሊጎዳ የመጣ ማንኛውም ኃይል ላይ መደራደር የለብንም።
ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖር በአንድነት መስራት እንደሚገባ አክሏል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ