የንብረት ታክስን በመጀመር የታክስ መሰረትን ማስፋት የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ይሆናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የንብረት ታክስን በመጀመር የታክስ መሰረትን ማስፋት የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ይሆናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ሰኔ 25/2014 (ኢዜአ) የንብረት ታክስን በመጀመር የታክስ መሰረትን ማስፋት የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ2015 በጀት አመት 70ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጿል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የ2014 በጀት አመት የግብር ማሳወቂያ ወቅት ማስፈፀሚያ ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች፣ ግብር ከፋዮችና ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የተለያዩ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የተውጣጡ ሰራተኞች ተገኝተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የገቢ አሰባሰብ እያደገ መምጣቱን አንስተው የገቢ አቅም እያደገ የታሰበውም መሳካቱ ይቀጥላል ብለዋል።
የገቢ እድገት መረጋገጥ የበጀት እድገትን በማምጣት የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመመለስ አቅምን ያሳድጋልም ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ገቢ የማመንጨት አቅም አሁን እየተሰበሰበ ካለው በላይ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ገቢን ለማመንጨት አቅምን ማጠናከርና ማደራጀት ብሎም የገቢ ሰብሳቢ መስሪያቤቶችን ማቀናጀት ይገባል ብለዋል።
"የልማት ፍላጎታችን ትልቅ ነው፤ይህንን የምናሳካው ተቀናጅተን የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመንና ፍትሃዊ በማድረግ ነው" ብለዋል ከንቲባዋ።
በመጪው በጀት አመት በገቢ ስርዓት ውስጥ ያለው ግብር ከፋይ ወቅቱንና ህጉን ጠብቆ እንዲከፍል በማድረግ ፍትሃዊነትን ማስፈን የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል።
የታክስ መሰረቱን በማስፋት ወደታክስ ስርዓት ያልገቡትን ማስገባትና የንብረት ታክስን መጀመር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው ቢሮው ለዚህ ራሱን ማዘጋጀት አለበት ብለዋል።
ቢሮውን በሰው ኃይል፣ በግብአትና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራን ባለድርሻ አካላት መደገፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ፤ በጠናቀቀው በጀት አመት ከማዘጋጃቤታዊ ገቢዎችና ከታክስ ለመሰብሰብ የታቀደው 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሰው በ11 ወራት 51 ቢሊዮን ብር ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ለዘንድሮ በጀት አመት ከያዘውና በምክር ቤቱ ይፀድቃል ተብሎ ከሚጠበቀው 100 ቢሊዮን ብር በላይ የከተማዋ በጀት ውስጥ 70 ቢሊዮኑ በቢሮው የሚሰበሰብ መሆኑንም ገልፀዋል።
በ2014 በጀት አመት የግብር ማሳወቂያ ወቅት 29 ነጥብ 5 ቢሊዮን የእቅዱን 42 በመቶ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው የተናገሩት።
ለእቅዱ መሳካት የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የቢሮውን የሪፎርም ስራ ማጠናከር፣ አሰራርን ማዘመን፣ ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠትና የህግ ማስከበር ስራን ማጠናከር የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በአፈፃፀማቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ ሰራተኞች ከ5 ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር ቦንድ ሲሸለሙ ለቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ደግሞ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።