ኢትዮጵያውያን ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን ለሀገራቸው ሰላም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን ለሀገራቸው ሰላም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል
ሰኔ 25 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን ለሀገራቸው ሰላም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ በባለሃብቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ትብብር የተመሰረተው የሰላምና ልማት ፎረም ገለጸ።
'ኢንተርፕሬኒያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት' የተሰኘው የሰላምና የልማት ፎረም ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ዛሬ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ የፎረሙ የበላይ ጠባቂዎች የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የችግኝ ተከላው "ኑ ሰላምን እንትከል፤ ኑ እርቅን እንትከል፤ ኑ እድገትን እንትከል፤ ኑ እህትማማችነትንና ወንድማማችነትን እንትከል፤ ኑ እንወያይ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትና የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ የሰላምና ትብብር ፎረሙ ለሰላም ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር በአረንጓዴ አሻራ የበኩሉን ለመወጣት እየሰራ ነው ብለዋል።
"ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ በአግባቡ ይረዱታል" ያሉት ዶክተር ሙላቱ፤ ሰላም ለሀገር ህልውና ለኢኮኖሚ እድገትና ለዜጎች ወጥቶ መግባት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሰላምና ልማት ፎረም የበላይ ጠባቂ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያውያን ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን ለሀገራቸው ሰላም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ጥላቻን በማስወገድ በመቻቻልና በመወያየት ችግሮችን በመፍታት በአብሮነት መኖርን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
የሰላምና ልማት ፎረምም የችግኝ ተከላውን ሲያከናውን "ኑ ሰላምን እንትከል" የሚል ጥሪ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህም ሰላምን በማስፈን ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና መሰረት እንጣል በሚል መነሻ ነው ብለዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ብዙ ተምሳሌትነት ስላለው በአረንጓዴ አሻራው የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ አለብን ብለዋል።
የኮሚሽኑ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ሰላም ዙሪያ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያውያን በማያግባቧቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንዲወያዩና እንዲግባቡ ይሰራል ነው ያሉት።