ቀጥታ፡

የኦሮሞ ሴቶች የእርቅና የሰላም ተምሳሌት በሆነው ”ሲንቄ” ባህል ላይ ያተኮረ የምርምር መጽሐፍ ተመረቀ

ሰኔ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኦሮሞ ሴቶች የእርቅና የሰላም ተምሳሌት በሆነው ”ሲንቄ” ባህል ላይ ያተኮረ የምርምር መጽሐፍ ዛሬ ተመርቋል።

መጽሐፉ “THE ESSENCE OF SINQE/SIQQO CULTURAL SYSTEM AND ITS ROLE IN THE OROMO COMMUNITY ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋራ በጋራ ያሳተሙት ነው ተብሏል።

በምርቃቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ እንደገለጹት፤ “ሲንቄ” ሴቶች ነጻነታቸውንና መብታቸውን የሚያስከብሩበት፤ ማህበራዊ ኃላፊነት የሚሸከሙበት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡

መንግሥት እንደ "ሲንቄ" ያሉ ባህሎችን የመጠበቅና የማበልጸግ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ በማካተት ለትውልዱ ማሳወቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የምርምር ተቋማትም ባህላዊ እሴቶችን በማጥናት ሀገራዊ ፋይዳቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ “ሲንቄ” የሴቶችን መብትና ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ባህል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ ተቋማት ሊበረታቱ እንደሚገባ በመጠቆም።
ሚኒስቴሩ የፖሊሲ ክለሳ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በክለሳው ውስጥ በሲንቄና ሌሎች ባህሎች ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በመጽሐፉ ዝግጅት ሂደት የተሳተፉት ወይዘሮ ወይንሸት ሀብተማሪያም "ሲንቄ" ባህል በስፋት በሚተገበርባቸው በኦሮሚያ አራት ዞኖች ጥናት በማካሄድ መጽሐፉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የመጽሐፉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መታተም የኢትዮጵያን ባህል ለዓለም ከማስተዋወቅ በላይ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ በርካታ ባህሎችን ለማበልጸግና ለማሳደግ መነሳሳትን ይፈጥራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም