ቀጥታ፡

የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ዳግም እያገረሸ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል- የህክምና ባለሙያዎች

ሰኔ 24/2014/ኢዜአ/ ህብረተሰቡ ዳግም እያገረሸ በሚገኘው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ተጋላጭ እንዳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የህክምና ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየተባባሰ ቢሆንም ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እየተገበረ እንዳልሆነ መግለጹ ይታወሳል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው ካለፈው አንድ ወር ወዲህ የኮቪድ ወረርሽኝ እየጨመረ  መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ይህም ዜጎችን ለሞት እና ለከፋ ህመም ተጋላጭ የመሆን እድላቸውን እያሰፋ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ሲያደርግ የነበረው ጥንቃቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከፍተኛ ቸልተኝነት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ ለቫይረሱ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ቢሆንም  እስካሁን ክትባቱን የወሰደው ህዝብ ቁጥር ከ30 በመቶ እንደማይበልጥም ነው የገለጹት።

የአንስቴቲስት ባለሙያዋ ሲስተር እንዳለች አባተ  በበኩላቸው ህብረተሰቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንደጠፋ ተደርጎ የሚናፈሰው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ነው ያሉት።

የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑን መገንዘብና ከጤና ተቋማት የሚወጡ ጠቃሚ መረጃዎችም በአግባቡ በመከታተል የቅድመ መከላከያ ጥንቃቄዎችን ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ወረርሽኙ በግለሰብ ጤናና በሀገር ላይ  እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ በመረዳት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ በሀሌሉያ ሆስፒታል ቺፍ አንስቴቲስት የሆኑት ዮሀንስ ተገኔ  ናቸው ፡፡

ዶክተር ተግባር ይግዛው ዜጎች በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡ  የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ቤተሰባቸውን እና ማህበረሰባቸውን ከአደጋ ሊታደጉ እንደሚገባ  ተናግረዋል።

በተለይም ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውና በእድሜያቸው የገፉ ሰዎችን ከሞት ለመታደግ ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን በአግባቡ መጠቀም፣ ንጽህናን መጠበቅ፣ ክትባቱን መውሰድ ያስፈልጋል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም