በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ሊሰራ ይገባል - አቶ ኡሞድ አጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ሊሰራ ይገባል - አቶ ኡሞድ አጁሉ
ጋምቤላ፤ ሰኔ24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።
የክልሉ ምሁራን በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይት መድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉ ህዝብ የሸኔ፣ የጋነግና የህወሓት ሴል የሽብር ቡድኖችን እኩይ ድርጊት በመዋጋት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በአንድነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የሽብር ቡድኖቹ ተላላኪዎች ሰሞኑን በጋምቤላ ከተማ ሞክረውት የነበረው የጥፋት ድርጊት በጸጥታ ኃይሎችና በህዝቡ የተቀናጀ ጥረት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የጥፋት ቡድኖች የተለመደውን ከፋፋይ አጀንዳቸውን በመጠቀም ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ለማተራመስ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህዝቡ አንደነቱን በማጠናከር የሽብር ቡድኖችን እኩይ ሴራ በመመከት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክሮ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በከተማው አስቸጋሪ የሆነውን የሌብነትና የዘረፋ ወንጀሎች በመከላከል ረገድም እንዲሁ የህዝቡ ትብብሩን ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዋይ ጆክ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኖቹ ባለፈው ወደ ጋምቤላ ከተማ ለመግባት ሙከራ ያደረጉት በከተማው በሚገኙ ሴሎቻው አማካኝነት ነው ብለዋል።
በጋምቤላ ከተማ መሽገው ለሽብር ቡድኑ መረጃ፣ ስንቅና ሌሎች ድጋፎችን የሚያቀብሉ አካላትን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ ረገድ ህዝቡ ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በሰጡት አስተያየት፤ የጋነግ፣ የሸኔና የህወሓት የሽብር ቡድኖች የተቀናጁት በውጭ ሀገር ከሚላላኳቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች "ፍርፋሪ ለመልቀም"ያደረጉት ያልተቀደሰ ጋብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
የእነዚህን የሽብር ቡድኖች እኩይ ሴራ ለማምከን በየአካባቢው የሚገኙ ሴሎቻውን ጭምር በመለየት ህጋዊ እርምጃ መውስድ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሰላም የሁሉም መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ ምሁር ኡቻላ ኡጁሉ ናቸው።