ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በ400 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ሰኔ 24/2014/ኢዜአ/ በአገር አቀፍ ደረጃ በ400 ጤና ጣቢያዎች ላይ በተደራጀ መልኩ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር "የእናቶች እና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ጥራት ያለው አገልግሎት ማበርከት ያስፈልጋል" በሚል መሪ ሃሳብ 15ኛውን ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡

በዚሁ ጉባኤ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በአገር አቀፍ ደረጃ  ከወሊድ ጋር የተያያዘ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ከ3 እስከ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም አገልግሎቱን ሳያገኙ ለውስብስብ የጤና እከል የሚዳረጉና የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በተለይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እንደ አገር የቀዶ ህክምና አገልግሎትን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን  አክለዋል።

ሚኒስቴሩ ከማህበሩ ጋር በመቀናጀት የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡  

በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ በ400 ጤና ጣቢያዎች ራሱን የቻለ የቀዶ ሕክምና መስጫ ህንጻ በመገንባት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡  

ማህበሩ  በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን  የማብቃት ሥራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ልዑልዓየሁ አካሉ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች አስፈላጊውን እውቀት ይዘው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ የማብቃት ሥራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የሙያ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የአንስቴቲስቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ከአንድ ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፤ ጉባኤውም  በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ መሆኑን ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም