የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመስከረም 4 ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመስከረም 4 ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል
አዲስ አበባ መስከረም 2/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ከመስከረም 4 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን እንደሚያካሂድ አስታወቀ። የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከመስከረም 4 ቀን ጀምሮ ምክር ቤቱ በሚያካሂደው ስብሰባ ባለፈው ሳምንት በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተገመገሙና ለምክር ቤቱ እንዲቀርቡ የተወሰኑ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል። ምክር ቤቱ ድርጅቱ ከመስከረም አጋማሽ በኋላ በሚካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የሚቀርብ ሪፖርት ላይ እንደሚወያይም ተጠቁሟል። በተጨማሪም በወቅታዊ ድርጅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡