የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው-የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው-የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24 ቀን 2014(ኢዜአ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ረዥም ዘመናትን የተሻገሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚሰራ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሙ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትውውቅ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራውን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መሸጋገሩን በቅርቡ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።
ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁሉም ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት የሲቪል ማህበራት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ቁልፍ ሚና ለመወጣት ዝግጁ ናቸው ።
በተለይ ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማንቃት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ተሳትፎአቸው የጎላ እንዲሆን ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ማህበራቱ የሀገራዊ ምክክሩ ባለቤት የሆነው የህብረተሰብ ክፍል በምክክሩ ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለምክክሩ ስኬት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሮች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ሄኖክ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በስሩ ከ4 ሺህ በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ይዟል፡፡