ቀጥታ፡

አንድነታችንን በማጠናከር የህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ለማስተጓጎል የሚሞከሩ ሴራዎችን መመከት ይገባል-ምሁራን

ሰኔ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንድነታችንን አጠናክረን የህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስራን ለማስተጓጎል የሚሞከሩ ሴራዎችን መመከት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ተናገሩ።

ከግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስራ በተጓዳኝ የዲፕሎማሲ ስራዎች በተደራጀ መልኩ ሊከናወኑ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

በአረቡ ዓለም የሚነዙ የተዛቡ ትርክቶችን በመሞገት የሚታወቁት የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ግብጾች የዓባይን ጉዳይ በተመለከተ ከደቂቅ እስከ ልሂቅ ባሉ ትውልዶቻቸው ላይ በልዩ ትኩረት ሰርተዋል ይላሉ።

ለናይል ወንዝ ከፍተኛውን ድርሻ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ግን ያላትን እውነት በዲፕሎማሲው መስክም ሆነ በስርዓት ትምህርቷ በማካተት ትውልድ ላይ ከመስራት አኳያ ይሄ ነው የሚባል ስራ አለመስራቷን ያስረዳሉ።

በዚህም ግብጽ ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ተጠቃሚነት እንዳይኖራት ከወታደራዊ ወረራ ጀምሮ ያልፈነቀለችው ድንጋይ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡

በአንጻሩ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ በራሷ አቅም ዐባይን ገድባ የመጠቀም ጉዞዋን አሃዱ ብላ መጀመሯን ያነሳሉ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 40 በመቶው ሲደርስ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግንባታውን ማጠናቀቅ እንደምትችል የተገነዘበችው ግብጽ መሰረተ ቢስ የሆኑ ጩኸትና እስከ ጸጥታው ምክር ቤት የደረሰ መልከ ብዙ ጫናዎችን ለማድረግ መጓዟን ያወሳሉ።

የግብጽ ምሁራን ከግድቡ ግንባታ ጥራትና ከሙሌት ጋር በማያያዝ የሚያነሷቸው ሙግቶች ቢከሽፉባቸውም፤ አሁን ላይ ደግሞ ሶስተኛው ዙር ሙሌት ሲቃረብ ሌሎች የመከራከሪያ ነጥቦችን እየመዘዙ አሉባልታ መንዛት ጀምረዋል ብለዋል።

የግብጽ ፍራቻ ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ የውሃ እጥረት ይገጥመኛል የሚል አለመሆኑን ተናግረዋል።

ይልቁንም በሀገሪቱ 30 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ያደረጉ የሳዑዲና ኤምሬትስ 7 ሺህ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ የሚል ስጋት በግብጽ በኩል መኖሩን ጠቅሰዋል።

የግብጽና መሰል የአረብ አገራት ሚዲያዎች ግድቡን አስመልክተው የሚነዙትን የተዛባ መረጃ የሚያጋልጡትና የሚሞግቱት ዑስታዝ ጀማል በሽር በበኩላቸው ከአረቡ ዓለም ጋር ያለን ችግር ዋናው ውሃ ነው ይላሉ።

በዚህም ግብጽ ኢትዮጵያን ከዓረቡ ዓለም ጋር ለማጣላት "ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጭቁን እንደሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር እንደምትሰራ እንዲሁም ግድቡ ከተገደበ ወደ ግብጽ ውሃ እንደማይፈስ" በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃዎች ስታሰራጭ መቆየቷን ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ሲጀምር የውሃ መጠን ቀነሰብኝ በማለት ሀሰተኛ ጩኽት ቢያሰሙም በተመሳሳይ ወቅት ከመጠን ያለፈ ውሃ እንዳጥለቀለቃችው አስታውሰዋል፡፡

የግብጽ ፍላጎት የውሃ መጠን ይቀንሳል ሳይሆን የወደፊት ፕሮጀክቶቿን እውን እስክታደርግ ኢትዮጵያ በድህነትና በርሀብ እንድትቀጥል በመሻት እንደሆነ ያነሳሉ።

ለዚህም በየጊዜው ኢትዮጵያን በተለያዩ አጀንዳዎች በመጥመድ ተጽዕኖዋን ለማሳረፍ አማራጮችን እየተጠቀመች መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም ሰሞነኛውን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዘግብና የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግሮችን ስታጯጩህ እንደነበር ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የሩስያ እና የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ በጋዝ እጦት ለተመታችው አውሮፓ ግብጽ ከኳታር ጋር በመሆን ክፍተቱን እንሞላለን በሚል እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልጸው፤ በምላሹም የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርግ ትፈልጋለች ብለዋል።

በቅርቡ የወጣው የአውሮፓ ሕብረት "የግብጽ የውሃ ድርሻ መነካት የለበትም" የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

ግብጽ ከጥንት ጀምሮ የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም ስትከውነው የነበረውን አገር የማተራመስ ስትራቴጂ ለማምከን ኢትዮጵያ ውስጣዊ ቀዳዳዎቿን መድፈን እንዳለባትም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ግብጽ በየጊዜው ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለማስገባት የምታመጣቸውን አማራጭ አጀንዳዎች ለመቋቋም ከወዲሁ ብርቱ ዝግጅት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም