ቀጥታ፡

የከተማ ግብርና በሙያዊ እውቀት ታግዞና የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ እየተሰራ ነው -- የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ

ድሬዳዋ ሰኔ 24/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የከተማ ግብርና ልማት ውጤታማና የስራ እድል ምንጭ እንዲሆን በዘርፉ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ።

ዩኒቨርሲቲው የተቀናጀ የከተማ ግብርናን በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅት አጠናቋል፡፡

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ  ዘርፉን በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር በተዘጋጀው የካሪኩለም መነሻ ፅሁፍ ላይ የዩኒቨርሲቲው ሙሁራንና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ያሳተፈ ውይይት ተደርጓል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም እንዳሉት የከተማ ግብርና በሙያና በእውቀት ታግዞ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት የመደገፍ አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ፡፡          

የተቀናጀ የከተማ ግብርና እንቅስቃሴዎች ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ ባለሙያዎችን ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ለማስተማር የሥርዓተ-ትምህርት ቀረፃ ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

ትምህርትና ስልጠናውን ውጤታማ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የከተማ ግብርና ሰርቶ ማሳያ ማዕከል መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ድሬዳዋና የምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ለተቀናጀ የከተማ ግብርና ሥራ ምቹ ሥነ-ምህዳር መኖሩን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ስነድ ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ቃሶ ናቸው፡፡

ዘርፉ በእንስሳትና ዶሮ እርባታ፣በከተማ ፅዳትና ውበት፣ ተፈጥሯዊ የመሬት ለምነት ማስጠበቅ ምርታማነትን ዘላቂ በማድረግ፣ በትንሽ ቦታ የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በተዘጋጀው ሰርቶ ማሳያ  ከማስተማሪያነት በተጨማሪ  የአከባቢው ማህበረሰብ ተግባራዊ እውቀት ይቀሰሙበታል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሳቲው የሚጀመረው ትምህርት እንደሀገር እተተገበረ ያለው የከተማ ግብርና ለተማሩ ወጣቶች ጭምር ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥርበት  መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ድሬዳዋ ለተቀናጀ ግብርና በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልፀው ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማገዝ  የተጎዳውን ሥነ-ምህዳር እንዲያገግም ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ይርዳው ደረጃ በበኩላቸው የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀው የከተማ ግብርና በቤተሰብ ደረጃ የሚስተዋለውን የምግብ ክፍተት የሚደፍንና የዋጋ ንረትን የሚያረጋጋ በመሆኑ በቅንጅት ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ሙሁራን የሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራሮች ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ጥረት ለውጤት እንዲበቃ  በጋራ  እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም