ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት አራተኛው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ በመጪው ጥቅምት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት አራተኛው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ በመጪው ጥቅምት ይካሄዳል
ሰኔ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት አራተኛው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ በመጪው ጥቅምት እንደሚካሄድ የውድድሩ አዘጋጆች ገለጹ፡፡
ውድድሩ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ''አብሮነት መሻል ነው'' በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፤ ውድድሩ በአጠቃላይ 5 ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ እንዳሉት፤ ውድድሩ በአሜሪካ የሚኖሩ አፍሪካውያንን ለማቀራረብና ለተለያዩ በጎ ስራዎች ገቢ ለማሰባሰብ ያለመ ነው።
በመርሃ-ግብሩም ለአገራቸው የጎላ አስተዋፅኦ ላደረጉ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እውቅና ሽልማት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ የአትሌቲክስ ስፖርት ባለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግራለች፡፡
ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት የራሱን አሻራ እያሳረፈ መሆኑን ገልጻ፤ ውድድሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና አለው ብላለች።
ውድድሩ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአካል በመገኘት ድጋፏን እየገለጸች መሆኑን አስታውሳ፤ ውድድሩ ትውልደ ኢትዮጵያን ህጻናት ባህላቸውን እንዲያውቁ ጥሩ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች።
በውድድሩ 5 ኪሎ ሜትሩን ለሚያጠናቅቁ ተሳታፊዎች የቶዮታ ተሽከርካሪ ተሸላሚ የሚያደርግ እጣ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
በዝግጅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን www.africanrun.com ድረ -ገጽ ተጠቅመው ምዝገባ ማካሄድ እንደሚችሉም ነው የተገለጸው።
በዝግጅቱ ላይ ከ20 በላይ ታዋቂ ኦሎምፒያኖች እና የዓለም ሻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ዝግጅቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኔሳ በቀለና መሰል ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወቃል።