ቀጥታ፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለ15ኛ ጊዜ አሸነፈ

ሰኔ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለ15ኛ አሸንፏል።

አዲስ አበባ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዷል።

የ30ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማጠናቀቂያ ጨዋታዎች ዛሬ በባህር ዳር ተካሄደዋል።

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ከተማን 4 ለ 0 በማሸነፍ በ65 ነጥብ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል።

ቶጎዋዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ፈረሰኞቹ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለ15ኛ ጊዜ ማንሳት ችለዋል።

በአንጻሩ አዲስ አበባ ከተማ በ32 ነጥብ 14ኛ ደረጃን በመያዝ ሰበታ ከተማና ጅማ አባ ጅፋርን ተከትሎ ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደ ሶስተኛው ክለብ ሆኗል።

በባህር ዳር ስታዲየም የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ በድሬዳዋ ከተማ 3 ለ 2 ተሸንፏል።ጋዲሳ መብራቴ፣ ሄኖክ አየለና አብዱራህማን ሙባረክ ለድሬዳዋ ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በረከት ደስታና በዛብህ መለዮ ለአፄዎቹ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ62 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ በ33 ነጥብ ከፕሪሚየር ሊጉ ከመውረድ ተርፏል።

በሌላኛው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 3 ለ 2 በማሸነፍ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም