በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ለተጎጂዎች ፍትሕን መስጠትና እርቅን መፍጠር ያስፈልጋል-አሜሪካ ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ለተጎጂዎች ፍትሕን መስጠትና እርቅን መፍጠር ያስፈልጋል-አሜሪካ ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ
ሰኔ 24 ቀን 2014(ኢዜአ) “በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሰላምን ለማምጣት ለተጎጂዎች ፍትሕን መስጠትና እርቅን መፍጠር አስፈላጊ ነው” ሲል መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው አሜሪካ ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ (ኤፓክ) ገለጸ።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው መገንዘብ አለበት ብሏል።
ኤፓክ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የተጀመሩ ጥረቶች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሞታቸውንና በ10 ሺዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን አመልክቶ "የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎችና አጋር ኃይሎች በትግራይ ጦርነቱ እንዲጀመርና ወደ ጎረቤት ክልሎች እንዲሰፋ ምክንያት" ሆኗል ብሏል።
የእነዚህ ኃይሎች ፍላጎት ወደ ስልጣን ዳግም ለመመለስና ኢትዮጵያን ወደ “ጨለማው ዘመን የአምባገነን አገዛዝ” እንድትመለስ ማድረግ ነበር ሲልም ኤፓክ አመልክቷል።
በአሜሪካና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ጦርነቱን አስመልክቶ እውነታውን ለዓለም የማሳወቅና ኢትዮጵያ ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ያደረገችውን ውጊያ እንድታሸንፍ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጿል።
አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ፣አፋርና ክልል ነዋሪዎች የፈጠረውን ሕመም በውል እንረዳለን ያለው ኤፓክ የአሸባሪው ኃይሎች ሕጻናትን ለውትድርና በማሰማራት፣ጅምላ ግድያ በመፈጸምና አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም አስከፊ የሚባሉ ድርጊቶች ፈጽሟል ብሏል።
ሆስፒታልና ትምህርት ቤቶች ጨምሮ ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አውድሟል ያለው መግለጫው አሸባሪው በፈጸማቸው ድርጊቶች የተጎዱ አብዛኞቹ ዜጎች እስካሁን ፍትሕ አላገኙም ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በአሁኑ ሰአት ራሱን እያደራጀና ተዋጊዎችን እየመለመለ ይገኛል ነው ያለው ኤፓክ በመግለጫው።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች አስቸኳይ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ሰአት አሸባሪው ሕወሓት ዳግም ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።
ኤፓክ የኢትዮጵያ መንግስትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከግምት ውስጥ ቢያስገቧቸው ባላቸው ነጥቦች አሸባሪው ሕወሓት በአፋር፣ትግራይና አማራ ክልሎች ለፈጸማቸው ድርጊቶች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆንና ተጎጂዎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክቷል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሕወሓት ትጥቅ በመፍታት በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈጽመውን የሽብር ድርጊት እንዲያቆም ጫና ማድረግ ይኖርበታል ብሏል።
በአማራና አፋር ክልሎች የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተገቢውን ትኩረት መስጠት መስጠት እንዳለባቸው ገልጾ አሜሪካንና ሌሎች አገራት “በኢትዮጵያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች እንዲያነሱና ነጻ የንግድ እድሎችን በድጋሚ እንዲጀምሩ” ጠይቋል።
የኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው የመወሰን መብትና ፍላጎት መከበር እንዳለበትም አመልክቷል።
ኤፓክ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት ለተጎጂዎች ተገቢውን ፍትሕ መስጠትና እርቅን መፍጠር ያስፈልጋል ሲል ገልጿል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ