ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ለሌሎች ምሳሌ መሆን አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ለሌሎች ምሳሌ መሆን አለባቸው
ሰኔ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በበኩሉ ጥላቻን በሚያሰራጩና ግጭትን በሚቀሰቅሱ መገናኛ ብዙኃን ላይ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝቧል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተግባር እንዲረጋገጥ መንግሥት የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡
በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ጣቢያዎች ጭምር በአገር ውስጥ በነጻነት እንዲሰሩ መደረጉ ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ ባለፉት አራት ዓመታት ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙትን ጨምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኢትዮጵያ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት በዘርፉ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ባለመጠቀም ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች እንደሚሉት፤ በተለይ ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ፍቅርና መቀራረብን መስበክ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአጭርና ረዥም ጊዜ ፕሮጀክቶች መምሪያ ኃላፊ መላከ ህይወት ቆሞስ አባ ወልደየሱስ ሰይፉ፤ ያልተገባ ዓላማን ይዘው ጥላቻንና መጠፋፋትን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃንን በጋራ መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ መንፈሳዊ መገናኛ ዘዴዎች ፍቅር፣ መቻቻልና አንድነትን መስበክ ለሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ሸኽ መሀመድ ሲራጅ በበኩላቸው፤ ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃን ማሰራጨት በእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮ የተከለከለ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
መልካሙን በመስበክ መጥፎን ማስቆም የሁሉም ኃይማኖቶች መሰረታዊ እሴት እንደሆነም እንዲሁ።
ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚቻለው የሀገር ሰላምና አንድነት ሲጠበቅ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ለሰላምና አንድነት በትኩረት መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልጸዋል።
አንዳንድ ኃይሎች መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም እነዚህን ችግሮች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንደሚጥሩም እንዲሁ፡፡
ከዚህ አኳያ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ለሕዝብ ሰላምና ለሀገር አንድነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ በዜጎች ሰላምና የአገር ደኅንነት ላይ አደጋ ለመጣል በሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡
አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ከሙያና አሰራር ውጭ መረጃን እንደሚያሰራጩ ሁሉ ኃይማኖትን መሰረት አድርገው ከተቋቋሙ የመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዳንዶቹ መሰል የሕግ-ጥሰት እንደሚፈጽሙም ነው ያነሱት፡፡
ከዚህ አኳያ ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ መገናኛ ብዙኃን የሚመሩበት ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ መገናኛ ብዙኃን ሰላምና ፍቅርን እንዲሁም በዜጎች መካከል መቀራረብ እንዲኖር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት፡፡