ቀጥታ፡

መንግስት ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እያከናወነ ካለው ተግባር በተጓዳኝ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

ሰኔ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እያከናወነ ካለው ተግባር በተጓዳኝ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት "ሐምሌ 19" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአቅም ደካሞችን ቤት የማደስ መርሃ-ግብር አስጀምረዋል።  

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በመጀመሪያ ዙር የቤት ዕድሳት መርሃ ግብር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የ12 ቤቶች ዕድሳትን እንደሚያከናውንም ተግልጿል፡፡

መርሃ-ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመርሃ ግብሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የአቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት እንደሚያድስ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት መርሃ - ግብርም ሚኒስቴሩ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት የማደስ ስራ ማከናወኑን አስታውሰዋል፡፡

መንግስት ከምንም በላይ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም መንግስት ሰላምን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት ሊደግፍ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የአቅመ ደካመ ዜጎችን መኖሪያ ከማደስ ጀምሮ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቆንጅት ደበላ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በተያዘው ክረምት 300 ቤቶችን ለማደስ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው፤ የእድሳት ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡  

የቤት ዕድሳት መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች፤ ከዚህ ቀደም በተለይ በክረምት ወቅት  በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ህይወታቸውን ይመሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግራቸውን ተገንዝቦ የመኖሪያ ቤታቸውን እድሳት በማስጀመሩ የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ያሥጀመረው የመጀመሪያ ዙር እድሳት መርሃ-ግብር ሲሆን፤ በቀጣይ የእድሳት ስራውን በሌሎች አካባቢዎች እንደሚያስጀምርም ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም