በደቡብ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ1 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጁ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ1 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጁ
ሀዋሳ ፤ ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ) በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር በክልሉ ከ1 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ሰኔ 27/2014ዓ.ም በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ በይፋ እንደሚጀምር ተመልክቷል።
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤" አሻራችን ለትውልዳችን፣አሻራችን ለልጆቻችን" በሚል መሪ ሀሳብ መረሃ ግብሩ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።
በዚህም ከ1 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለተከላ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል ።
በተለይም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚሰጡ የፍራፍሬ ችግኞች በልዩ ትኩረት መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ እነዚህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
ቀሪዎቹ ቡና ፣ዋንዛ ፣ጥድና የመሳሰሉ የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስና ለምነት ለመጨመር አቅም ያላቸው ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች መሆናቸውን አመላክተዋል።
የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ክልላዊ መረሃ ግብር በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ በይፋ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል።
ለተከላው የሚሆን የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅቶች አስቀድመው መጠናቀቁን ገልጸው፤ በአጠቃላይ ለአንድ ወር በሚቆየው በዚሁ የተከላ መርሃ ግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠናቸው ከ86 በመቶ በላይ እንደሆነ መረጋገጡን ያወሱት አቶ ኡስማን ፤ ካለፉት ዓመታት መልካም ተሞክሮ በመውሰድና ክፍተቶች በማስተካከል ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
ከዚህ ቀደም በተከናወነው ስራ የአፈር ለምነት በመመለስ የእንስሳት የመኖ ልማትና የውሃ መያዝ አቅም እንዲጨምር ከማገዙም ሌላ ምንጮች መፍለቅ መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ለግብርና ልማት ስራ መዘመንና ምርታማነት ማደግ አማራጭ መፍትሄ እየሆነ መምጣቱን አመላክተዋል።
ችግኝ መትከልና መንከባከብ የአካባቢን ስነምህዳርና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብና ማጽደቅ ላይም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል ።